ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን የሱማሞ አየር ማረፊያ ያለበትን የግንባታ ደረጃ ምልከታ አደረጉ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ፤ በወላይታ ዞን አረካ ከተማ አቅራቢያ በግንባታ ላይ የሚገኘውን የሱማሞ አየር ማረፊያ የግንባታ ፕሮጀክት ያለበትን የግንባታ ደረጃ የመስክ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን፤ ግንባታውን በተያዘለት ጊዜ ማጠናቀቅ እንዲቻል በቀጣይ ስራዎች ዙሪያም ከባለድርሻ አካላት ጋር መክረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በጉብኝቱ ወቅት ከዚህ ቀደም በተደረገ የመስክ ምልከታ፤ የአየር ማረፍያ ግንባታው መጀመርን ተከትሎ በግንባታ ዙሪያ ያሉ ችግሮችን በመለየት ፕሮጀክቱ ያለምንም መስተጓጎል ግንባታውን በፍጥነት ማከናወን እንዲቻል አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል፡፡

የዛሬው ምልከታ ዓላማም በተቀመጠው አቅጣጫ መሠረት የተከናወኑ ስራዎችን በመመልከት እንዲሁም የፕሮጀክቱ ግንባታ ያለበትን ደረጃ በመገምገም የአየር ማረፍያ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ እንዲጠናቀቅ ለማስቻል የቅርብ ድጋፍና ክትትል ለማድረግ እና በቅንጅት የተጀመሩ ስራዎችን ለማጠናከር ያለመ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

የአየር ማረፊያ ግንባታው ከዝግጅት ምዕራፍ ጀምሮ ለግንባታው በፍጥነት አለመጀመር ማነቆ የነበሩ ውስብስብ ችግሮችን ለመፍታት ብዙ ርቀት መከዱን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ችግሮችን በተቀናጀ አግባብ በመፍታት አሁን ላይ በሙሉ አቅም ወደ ግንባታ መገባት መቻሉ ትልቅ እምርታ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቱ በሙሉ አቅም ግንባታ ላይ ከመሆኑም በላይ ስራው በተሻለ ፍጥነት እና ጥራት በመከናወን ላይ መሆኑን በመመልከታቸው መደሰታቸውንም ገልጸዋል፡፡

የአየር ማረፊያ ግንባታው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ ለክልሉም ሆነ ለቀጠናው የጎላ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ይኖረዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት ለግንባታው በተያዘለት ጊዜ መጠናቀቅ አስፈላጊውን ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የፕሮጀክቱ ግንባታ ያለምንም መስተጓጎል በተጀመረው አግብባ በፍጥነት ተከናውኖ እንዲጠናቀቅ ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ግሩፕ ጋር በቅርበት በመሰራት ላይ ስለመሆኑም አስታውቀዋል፡፡ 

በክልሉ በተያዘው የ2018 የበጀት አመት በሁሉም ዘርፍ የተጀመሩ ውጤታማ ስራዎችን ከማጠናከር ባለፈ የጎላ ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸውን ፕሮጀክቶች ከዳር በማድረስ የተጀመረውን የብልጽግና ጉዞ የማጽናት ግብ ተጥሎ ወደ ስራ መገባቱን ያስታወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህም ውጤታማ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን አያይዘው ተናግረዋል፡፡  

በበጀት አመቱ በሁሉም ደረጃ በዋዛ የሚጠፋ ጊዜ ልኖር አይገባም ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተጀመረው አግባብ የክልሉ መገለጫ የሆነው ሰላምን በማፅናት ከመቸውም ጊዜ በላይ ኅብረትና ትብብርን አጠናክሮ በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ በመስራት የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መትጋት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

Leave a Reply