
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት አቅርበዋል፡፡



ርዕስ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው በትኩረት ከዳሰሱዋቸው ተግባራት መካከል፤ በክልሉ የፊስካል ፖሊስ ረገድ በገቢ አሰባሰብና የውስጥ አቅምን በማጎልበቱ ረገድ የተመዘገበው አመርቂ ውጤት ተጠቃሽ ነው፡፡
የክልሉ መንግስት የውስጥ አቅምን ለማጎልብት ለገቢ አሰባሰብ ስራው ልዩ ትኩረት ሰጥቶ ሲሰራ መቆየቱን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ የዉስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ከጊዜ ወደ ጊዜ በከፍተኛ ደረጀ ማደጉን ጠቁመዋል፡፡



በዚህ ረገድ፤ በ2018 የበጀት ዓመት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሃዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የክልሉን የወጪ ፍላጎት 75 ከመቶ በዉስጥ ገቢ ለመሸፈን በማለም በበጀት ዓመቱ ጠቅላላ ገቢ ብር 32,400,000,000 ለመሰብሰብ ታቅዶ መሰራቱን ጠቅሰዋል፡፡
በዚህም በበጀት ዓመቱ ከመደበኛ ብር 27,968,289,457 እንዲሁም ከማዘጋጃ ብር 4,386,278,489 በድምሩ ብር 32,354,567,946 ገቢ በመሰብብ የዕቅዱን ሙሉ በሙሉ በማሳካት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀው፤ ለስኬቱ ለገቢው ስኬት አመራሮችና ባለሙያዎች እና አስተዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡



ከዚህ ባለፈ በበጀት ዓመቱ ፍትሃዊ የሀብት ክፍፍልን ለማረጋገጥ ግልፀኝነትና ተጠያቂነት የሰፈነበት የአሰራር ሥርዓት በመዘርጋት ለዞን እና ከተማ አስተዳደር እርከኖች ለክልላዊ ፕሮግራም፣ ለዘላቂ ልማት ግቦች ማስፈጸሚያና ተያያዥ ጉዳዮች ጥቅል በጀት ተደልድሎ ጥቅም ላይ እንዲውል መደረጉንም ገልፀዋል።




