“የህዝባችንን ሀብት፤ ዕውቀትና ጉልበት በማቀናጀት በተደማሪ አቅም ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንሰራለን” ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከዞኑና ከሳውላ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እና አመራሮች ጋር በሰላም፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ ተወያይተዋል፡፡ 

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ ህዝባችን የሚያሳየን ፍቅር እና አክብሮት የኩራት ምንጭ ብቻ ሳይሆን ታላቅ ኃላፊነትና አደራ መሆኑን እንገነዘባለን፤ ይህንኑ እንደ ትልቅ አቅም ተጠቅመንም ህዝባችንን በማስተባበር ለተጨባጭ ውጤት እንተጋለን ሲሉ ተናግረዋል፡፡

የጎፋ ዞን በብዝኃነት የተዋበው ክልላችን ነፀብራቅ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዘመናት በተሻገረ አብሮነት የተሠናሠሉት የዞኑ ህዝቦች ድንቅ የሰላም፤ የትብብር፤ የወንድማማችነትና የአንድነት አኩሪ እሴቶች ባለቤት መሆናቸውን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ በአዲስ የስራ ባህል፤ በጊዜ የለንም መንፈስ ወደ ስራ የገባው የመደመር መንግስት፤ ብዝኃነትንና ፍትሃዊነትን ማዕከል ባደረገ መልኩ ክልሉ ያለውን ሰፊ ፀጋ በአግባቡ በመጠቀም ለክልሉ ህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ቁርጠኛ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡  

ቃላችንን ጠብቀን፤ በመደመር ዕሳቤና መርህ የህዝባችንን ሀብት፤ ዕውቀትና ጉልበት በማቀናጀት በተደማሪ አቅም ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ እንሰራለን ሲሉም አክለዋል።

እዚህ የተገኘነው ክብር ለመቀበል ሳይሆን ህዝብን በክብር ለማገልገል ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ ለላቀ ውጤት ከህዝብ ጋር በመወያየት ይበልጥ ተቀራርቦ በትብብር መስራት አስፈላጊ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በዚህ ረገድ ውይይቱ በዞኑ ህዝብና በከተማው ህብረተሰብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመለየት ባሻገር የልማት ትብብርን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መስራት የሚያስችል መግባባት ለመፍጠር ያለመ መሆኑን ገልፀዋል።

በውይይቱ የተነሱ የመሰረተ ልማት፤ የመልካም አስተዳደርና እና ተያያዥ ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ፤ በመካከለኛ እንዲሁም በረዥም ጊዜ ዕቅድ ለመመለስ ታቅዶ የሚሰራ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ አብራርተዋል።

በጎፋ ዞንና በሳውላ ከተማ ካለው ከፍተኛ አቅም አንጻር ብዙ መስራት ይጠበቃል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ በዞኑ ያሉ ፀጋዎችንና የመልማት አቅሞች በአግባቡ ለይቶ በማቀድ፤ የዞኑን ህዝብ የልማቱ ባለቤት ባደረገ መልኩ ተናቦና ተቀናጅቶ በጊዜ የለንም መንፈስ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል።  

የወጣቶች የስራ ዕድል ፈጠራ፤ የሳውላ ከተማ የኮሪደር ልማት የማስፋፋት፤ የአምራች ኢንዱስትሪ ዘርፉን የማነቃቃት እንዲሁም በቱሪዝም ዘርፍ ያሉ ያልተነኩ አቅሞችን በማልማት ዞኑንና ከተማ አስተዳደሩን ተመራጭ የቱሪዝም መዳረሻ ማድረግ ትኩረት ልሰጠው እንደሚገባም ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ዞኑና ከተማ አስተዳደሩ የህብረተሰቡን የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎች በብቃት በመፍታትና በአዲስ ዕቅድ ተጨባጭ ስራ በመስራት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የሚገባቸው መሆኑንም አሳስበዋል፡፡ 

በመንግስት ጥረት ብቻ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችና አዳጊ ፍላጎቶች ምላሽ መስጠት ስለማይቻል መላው የዞኑ ህዝብና የግሉ ዘርፍ የልማት ትብብሩን በማጠናከር የታለሙ ዘርፈ ብዙ የሰላም፤ የኢኮኖሚ ዕድገት እና የማህበራዊ ልማት ግቦች ከዳር እንዲደርሱ በማገዝ አሻራቸውን ማኖር የሚገባቸው መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ህዝባችን የሚያሳየን ፍቅር እና አክብሮት የኩራት ምንጭ ብቻ ሳይሆን ታላቅ ኃላፊነትና አደራ መሆኑን እንገነዘባለን፤ እንደ ትልቅ አቅም ተጠቅመንም ለተጨባጭ ውጤት እንተጋለን በማለት ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው፤፤ በጎፋ ዞን ያልተመለሱ የልማት ጥያቄዎች መኖራቸውን የክልሉ መንግስት ይገነዘባል ብለዋል።

ብልጽግና የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ብልጽግና ለማረጋገጥ ይሰራል ያሉት ኃላፊው፤ ከሕዝቡ ባገኘው ድጋፍና ፍቅር በጊዜ የለንም መንፈስ በአደራ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል።

Leave a Reply