
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለአሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ዲሽታ ጊና” የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለአሪ ብሄረሰብ የዘመን መለወጫ “ዲሽታ ጊና” በዓል በሰላም አደረሰን! አደረሳችሁ!
የአሪ ብሄረሰብ የራሱ ዘመን አቆጣጠር ቀመር ያለው፣ የቱባ ባህል እና ዘርፈ ብዙ የተፈጥሮ ፀጋ ባለቤት የሆነዉ በወረሃ ታህሳስ መጀመሪያ የሚያክበረው የአዲስ ዓመት የዘመን መለወጫ በዓል ነዉ ዲሽታ ጊና።
ከክልላችን ድንቅ እሴቶች መካከል አንዱ የሆነው “ዲሽታ ጊና በዓል” በብሔረሰቡ ባህልና ትውፊት መሠረት፤ አስቸጋሪው ወቅት ማለፉን በማብሰር ብሩህ ዘመንን በአዲስ መንፈስ የሚቀበሉበት እና ዓመቱ በሰላም ይጠናቀቅ ዘንድ ምኞትና ምስጋና ለፈጣሪ የሚያደርስበት የምስጋና በዓል ነው።
ዲሽታ ጊና በዓል የአንድነት፣ የሰላም፤ የአብሮነት፤ የመተሳሰብ እና የወንድማማችነት ተምሳሌት በዓል በመሆኑ ሌሎች ወንድም እህት ህዝቦች ጋር በአብሮነትና በአንድነት፤ የእርስ በእርስ ትስስርን በሚያጠናክር እና የወንድማማችነት እሴቶችን በሚያጎለብት መልኩ የሚከበር ድንቅ በዓል ነዉ።
አባቶች ያቆዩልንን ይህን ድንቅ እሴት፤ የአሁኑ ትውልድ በዓሉን ከነሙሉ ባህላዊ ትውፊቱ ጠብቆ በማቆየት ለቀጣይ ትውልድ በማሸጋገር ለወንድማማችነት ገዥ ትርክት ግንባታ እንድዉል የማድረግ ኃላፊነቱን ሊወጣ ይገባል።
የዘንድሮ በዓል እንደከዚህ ቀደሙ በአደባባይ ህብረ ብሄራዊ ውበታችንን በማጉላት በጋራ ማክበር የማይቻልበት ሁኔታ ውስጥ እንገኛለን። ይህም በዞኑ በተከሰተው እና የዜጎቻችንን ውድ ህይወት በቀጠፈው የማርበርግ ቫይረስ በሽታ ምክንያት ነዉ።
በዚህ በሽታ ህይወታቸዉን ላጡ ወገኖች ነፍሳቸዉን ፈጣሪ በአፀደ ገነት እንድያሳርፍ፤ ለመላ ቤተሰቦቻቸዉ በድጋሚ መጽናናትን እመኛለሁ።
ህብረተሰቡ ቫይረሱ መተላለፊያ መንገዶችን በመለየት ከበሽታው ራሱን እንዲጠብቅ እና የበሽታው ምልክት ሲመለከት ፈጥኖ ወደ ጤና ተቋም በመሄድ ራሱን እንዲከላከል ጥሪዬን አቀርባለሁ።
በቀጣይ ዓመት ይህ ጊዜ አልፎ በአደባባይ በታላቅ ድምቀት ላሻገረን ፈጣሪ ምስጋና በማቅረብ እንደምናከብር እምነቴ የፀና ነው።
በዓሉ የሰላም፤ የፍቅር፤ የአንድነትና የአብሮነት በዓል እንዲሆንልን እመኛለሁ!!
ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
መልካም በዓል!
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር




