ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የትንሣኤ በዓልን በማስመልከት ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡ ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው፡- ብርሃነ ትንሣኤውን ስናከብር ከመጓተት ይልቅ አብሮ መቆምን፤ ከመገፋፋት ይልቅ ትብብርን፤ ከመለያየት ይልቅ ህብረትና አንድነትን ይበልጥ አጠናክረን፤ ፈተናዎችን በፅናት በመሻገር ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የልማት ትልሞቻችን በጋራ በመረባረብ የኢትዮጵያን የመንሰራራት ጎዞ ለማፅናት በመነሣት ሊሆን ይገባል ብለዋል፡፡

የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ለመላው የክርስትና እምነት ተከታዮች እንኳን ለጌታችንና ለመድኃኒታችን ለኢየሱሰ ክርስቶስ የትንሣኤ በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!  

ብርሃነ ትንሣኤው ሞተ ሥጋና ሞተ ነፍስ የተሻረበት፤ መርገም የተወገደበት፤ ነፃነት የተገኘበት በመሆኑ፤ በክርስትና እምነት ተከታዮች ዘንድ በታላቅ ደስታና መንፈሳዊ ስሜት የሚከበር ደማቅ በዓል ነው፡፡    

በዓለ ትንሣኤው የዕርቅ፤ የይቅርታና የሰላም ተምሳሌትም ነው፡፡ በሰውና በፈጣሪ መካከል የነበረ የጥል ግድግዳ በአምላክ ይቅር ባይነት የፈረሰበት፣ ዕርቅና ሰላም ወርዶ አዲስ የምሕረት ምዕራፍ የተከፈተበት በመሆኑ በዓሉ ስከበር ቂም፤ ቁርሾና በቀልን በይቅርታ በመሻገር የምከበር ነዉ። 

ክርስቶስ ለሰው ልጆች ድኀነትና ፍጹም ሰላም ሲል ጽኑ መከራና ስቃይን ተቀብሎ ቤዛ የሆነበትን ሚስጢር በማሰብ የሚከበረው በዓል ፤ ሰላም ከፈጣሪ የተቸረን ፀጋ መሆኑን አውቀን፤ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላም ትብብራችንን የምናጠናክርበት አጋጣሚ መሆን ይኖርበታል፡፡ 

ብርሃነ ትንሣኤው የተስፋ፤ የፅናት እና የድል በዓል ነው፡፡ ክርስቶስ በሰሞነ ሕማማቱ የመከራን ቀንበር ተሸክሞ፤ በፈተና በመፅናት የተስፋውን ቃል ይጠበቅ ለነበረው አዳም ድኅነትንና ዘላለማዊ ህይወትን ያጎናፀፈበት የፅናትና የድል ተምሳሌት ነው፡፡ 

በዓለ ትንሣኤውን ስናከብር ከመጓተት ይልቅ አብሮ መቆምን፤ ከመገፋፋት ይልቅ ትብብርን፤ ከመለያየት ይልቅ ህብረትና አንድነትን ይበልጥ አጠናክረን፤ ፈተናዎችን በፅናት በመሻገር ለክልላዊና ሀገራዊ የሰላምና የልማት ትልሞቻችን በጋራ በመረባረብ የኢትዮጵያን የመንሰራራት ጎዞ ለማፅናት በመነሣት ሊሆን ይገባል፡፡  

የክርስቶስ ትንሣኤ የፍቅርና የእውነት ኃያልነት የተገለጠበት በመሆኑ ብርሃነ ትንሣኤውን ስናከበር፤ በጥላቻና በሀሰት ዘመቻዎች ሳንጠለፍ ፍቅርን በመስበክ፤ አብሮነትንና አንድነትን በማጠናከር እና የጋራ ሰላማችንን የበለጠ በመጠበቅ መሆን ይኖርበታል፡፡   

በዓሉ ከክርስቶስ የፍቅርና የሰላም መንገድ ትምህርት በመውሰድ በክልላችን ለክልላዊ የሰላምና የመቻቻል ተምሳሌት ራዕያችን ስኬት አብረን በመቆም ማስፈን የቻልነውን ሰላም ለማፅናት ከመቼውም ጊዜ በላይ በጋራ የምንነሣበት ሊሆን ይገባል፡፡   

ትንሣኤ የፍጹም ትህትናና የመታዘዝ ተምሳሌት ነው፡፡ በዓሉን ስናከብር ክርስቶስ ዓለምን የማዳን ታላቅ ገቢር በትህትና መፈፀሙን በማሰብ፤ በየተሰማራንበት መስክ ሀገራችንና ህዝባችንን በፍጽም ትህትናና ቅንነት ለማገልገል በመነሳት እንዲሆን አደራ ለማለት እወዳለሁ፡፡

አንድነትና ኅብረት፤ መደጋገፍና መረዳዳት በክርስትና ልዩ ስፍራ እንደሚሰጠው የእምነቱ አስተምህሮ ያስረዳል፡፡ በመሆኑም በዓሉን በትንሣኤ ልቦና ተነሥተን የመተሳሰብ፤ የመጠያየቅና የመደጋገፍ እሴቶችን በማንገብ፤ ያለንን ለለሌው በማካፈል፤ አቅመ ደካሞችንና ድጋፍ የሚሹ ወገኖችን በመደገፍ እና ራስን ለበጎ ተግባራት በማዘጋጀት ማክበር ይጠበቅብናል፡፡

በተለይ ትንሣኤው ለመልካም ስራ እንድንነሳ  የሚያደርግ መሆኑን ተረድተን፤ መረዳዳቱና መደጋገፉ በዕለተ ፋሲካው ሳይገደብ ተባብረን በያለንበት የተቸገሩ ወገኖችን በዘላቂነት ራሳቸውን እንዲችሉ ለማስቻል በመስራት ማክበር ይገባናል፡፡  

በድጋም መልካም የትንሣኤ በዓል!

ፈጣሪ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር

Leave a Reply