“በውስጥ ባንዳዎች እና በውጪ ባዳዎች ያጣነውን የወደብ ባለቤትነት በማስመለስ ዳግመኛ የአድዋ አርበኞች መሆን ይገባናል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት ለክልሉ የፖሊስ አመራሮች እና አባላት ከጂኦ ስትራቴጂ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና በሚል ሀሳብ የሚሰጥ ስልጠና ማስጀመሪያ መርሃ ግብር በወላይታ ሶዶ ከተማ ተካህዷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ ባስተላለፉት መልዕክት፥ ኢትዮጵያ ትላንት በዓለም ደረጃ የስልጣኔ ባለቤት፣ በጂኦ ስትራቴጂ የምትፈራ ከነበረችበት በውስጥና በውጪ በንዳዎች ምክንያት ያጣቸውን ታሪክ ለማስመለስ እየተሰራ ይገኛል ብለዋል።

ስልጠናውን የሚሰለጥኑ የፖሊስ አባላትም ሀገራችን ከጂኦ ስትራቴጂ ኩስምና ወደ ታደሰ ቁመና ለማሻገር እና ለማንኛውም ልዩ ሀገራዊ ተልዕኮ ዝግጁ ሊሆኑ እንደሚገባም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ በቀደምት ግዚያት የስልጣኔ ተምሳሌት የነበረች፣ የሰው ልጅ መገኛ፣ ዘመናዊ መሳሪያ ታጥቀው ሊገዙን የመጡትን በምኞት ያስቀረች የታላቅ ህዝብ ባለቤት ታላቅ ሀገር ናት ሲሉም አስገንዝበዋል።

የጂኦ ስትራቴጂያዊ ቁመናችን የሚለካው እንደ ሀገር ባለን የልማት ትልም ስኬቶች ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ የትልልቅ ፕሮጀክቶች መጠናቀቅ ኢትዮጵያ በተስተካከለ ቁመና እንድትገኝ የሚስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

ቀጣይነት ያለው የኢኮኖሚ አቅም ለመገንባት የውስጥ ፀጋዎችን አሟጦ መጠቅም እንደሚገባም ገልፀው፥ ለዚህ ደግሞ ከግድቡ ወደ ወደብ የምናደርገው ጉዞ ወሳኝ ነው ሲሉ በአጽንኦት ገልጸዋል።

ጂኦ ስትራቴጂው የፈጠረልንን ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም፥ በውጪና በውስጥ ባንዳዎች እንዲሁም ባዳዎች ያጣነውን ወደብ በማስመለስ እና ሀገራችንን ወደ ብልጽግና በማሸጋገር ዳግማዊ የአድዋ አርበኞች ልንሆን ይገባል ሲሉም አሳስበዋል።

ኢትዮጵያ ወደቡን በጋራ ተጠቅሞ በጋራ የማደግ ስትራቴጂ በመንደፍ እየሰራች እንደምትገኝም ርዕሰ መስተዳድሩ ጨምረው አስረድተዋል።

ከዚህ ቀደም የሀሳብ ኩስምና ከነበረበት ሰርቶ የሚያሰራ መሪ በመኖሩ ምክንያት ትልልቅ ፕሮጀክቶች መጀመራቸው እንኳን ሳይታወቅ የሚጠናቀቁበት ግዜ ላይ እንደምትገኝ በመግለጽ አድንቀዋል።

ለኢትዮጵያ ሰላም፤ ብልጽግና እና ልዕልና ሀገሪቱን ወደ ነበረችበት ገናናነት ለመመለስ የዓላማ ፅናት ያለው የፀጥታ ሃይል አስፈላጊ መሆኑንም ገልጸው፤ ሰልጣኝ የፖሊስ አባላት የኢትዮጵያን ወቅታዊ ብሔራዊ ፍላጎት በውል በመገንዘብ ለስኬታማነቱ ሊተጉ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የክልሉንም ሆነ የሀገሪቱን ሰላም ለማፅናት የፖሊስ አባላት ሕገ-መንግስቱን በመጠበቅ፤ የሕግ የበላይነት የማስከበር ሚናቸውን ይበልጥ ማጠናከር አለባቸው ሲሉም አስገንዝበዋል።

የጂኦ ስትራቴጂ ኩስምና ምንጩ ነጠላ ትርክቶች ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ እርስ በርስ በመባላት ሀያል መሆን ሲንችል እንዳንሆን የተሰራብን ሴራን ማስቆም ይገባል ብለዋል።

ለኩስምና ካበቁን ፈተናዎች ውስጥ ከነጠላ ትርክቶች በተጨማሪ የመዋቅር መዳከም እና የኢኮኖሚ ድቀት መሆናቸውን ገልፀው፥ ሁለንተናዊ ሪፎርም በማድረግ ተቋማትን የማጠናከር ስራ በመስራት ለውጥ መምጣቱን አስረድተዋል።

ውጤት በመጣ ቁጥር ጠላትም ስልቱን ቀይሮ ይመጣል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፥ በተለይ የውስጥ አንድነታችንን በመሸርሸር እና ግጭት በመፍጠር ኢትዮጵያን ለማዳከም ዛሬም የማይተኙ ሃይሎች መኖራቸውን ገልጸዋል።

በመሆኑም የፀጥታ መዋቅሩን በአካል፥ በአዓምሮ እና በስነልቦና የጠነከረ፣ የአሸናፊ ስነልቦና የተላበሰ እና ለማንኛውም ሀገራዊ ተልዕኮ ዝግጁ የሆነ የፀጥታ ሀይል እንዲሆን ማብቃት ይገባል ሲሉ በማሳሰብ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።

Leave a Reply