
ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ለይፋዊ የስራ ቆይታ በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል፤ በጎፋ ዞን፤ በክልሉ ሳውላ ማዕከል ገብተዋል፡፡



ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በሰላምና በብዝኃነት ተምሳሌቷ ሳውላ ከተማ ሲደርሱ፤ በክልሉ የሳውላ ማዕከል ከፍተኛ የስራ ኃላፊዎች፤ በጎፋ ዞን እና በሳውላ ከተማ አስተዳደር ከፍተኛ አመራሮች፤ በሀገር ሽማግሌዎች እንዲሁም በከተማው ነዋሪዎች እጅግ ደማቅ አቀባበል ተደርጎላቸዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ ለይፋዊ የስራ ቆይታው ሳውላ መለስተኛ አየር ማረፍያ መድረሳቸውን ተከትሎ እስከ ሳውላ ከተማ በተንቀሳቀሱባቸው ስፍራዎች ሁሉ መላው የአካባቢው ህብረተሰብ እና የከተማው ነዋሪ እጅግ ባማረና በደመቀ መልኩ ልባዊ ፍቅሩንና ጥልቅ አክብሮቱን ገልጾላቸዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የመደመር መንግስት ምስረታን ተከትሎ ከዚህ ቀደም በወላይታ ዞን፤ በወላይታ ሶዶ ማዕከል፤ በጋሞ ዞን፤ በአርባምንጭ ማዕከል እንዲሁም በጌዴኦ ዞን፤ በዲላ ማዕከል እጅግ ደማቅ የሆነ ህዝባዊ አቀባበል የተደረገላቸው መሆኑም የሚታወስ ነው፡፡






ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በጎፋ ዞን ቆይታቸው ከዞኑና ከሳውላ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እና አመራሮች ጋር በሰላም፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ የሚመክሩ ይሆናል።



ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በሁሉም ዘርፍ ለሚከናወኑ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎች ውጤታማነት ከህዝቡ ጋር ተወያይቶ የጋራ መግባባት በመፍጠር የልማት ትብብሩንና ተሳትፎውን ማሳደግ መሰረታዊ መሆኑን በማመን በተለያዩ ዞኖች ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በመወያየት ላይ ይገኛሉ፡፡



የዚሁ አካል በዛሬው ዕለት በሳውላ ከተማ ከጎፋ ዞንና ከሳውላ ከተማ ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በመወያየት በቀጣይ የልማት ተግባራት ዙሪያ የጋራ መግባባት ይፈጥራሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡










