“አካባባዊነትንና ከፋፋይነትን በማስወገድ በወንድማማችነት እሴቶች የተገነባ የህዝቦች አንድነትን ማጠናከር ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) ከኦሪ እና ከደቡብ ኦሞ ዞን ከተወጣጡ ከተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች ጋር በጂንካ ከተማ ተወያይተዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በጅንካ ከተማ በህብረተሰቡ ለተደረገላቸው እጅግ ደማቅ አቀባበል ልባዊ ምስጋና በማቅረብ፤ ህዝቡ የሰጠንን አደራ በአግባቡ ለመወጣት ተግተን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

ውይይቱ በሁለቱ ዞኖቹ በህብረተሰብ የሚነሱ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ከመለየት ባሻገር የልማት ትብብርን በማጠናከር ለዘላቂ ሰላምና ልማት በጋራ መስራት የሚያስችል መግባባት ለመፍጠር ያለመ መሆኑንም ገልፀዋል።

ኦሪ እና ደቡብ ኦሞ የኢትዮጵያዊያን ጌጦች ናቸው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አከባቢው የተለያየ ብዝኃ ማንነት ያላቸው ህዝቦች በአንድ ላይ በፍቅር ተከባብረው፤ ተዋደውና ተቻችለው የሚኖሩበት የመቻቻልና የፍቅር ተምሳሌት ህዝቦች መኖሪያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ይህን የአብሮነት፤ የአንድነት፤ የሰላምና የወንድማማችነት እሴት ጠብቀው ላቆዩ የአከባቢው ህዝቦች ምስጋና ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡

አካባቢው የታታሪዎችና የጀግኖች ህዝቦች መኖሪያ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሚቀጥሉት አምስት አመታት ይሄን አካባቢ ወደ ልማትና ብልፅግና ማዕከልነት ለመቀየር በትኩረት የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

የኦሪና የደቡብ ኦሞ ዞን ሀብትና እምቅ አቅም ለኢትዮጵያ የብልፅግና ተስፋ መሆን ይችላል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የብዝኃነት፤ የፀጋ እና የተስፋ ምድር በሆኑት ሁለቱ ዞኖች ያሉ ሀብቶችን ወደ ውጤት በመቀየር የአካባቢውን ህዝብ ባለው ፀጋ ልክ በማልማት ከድህነት ለማውጣ በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

በአካባቢው በትምህርት ላይ የቅድሚያ ቅድሚያ በመስጠት በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ የቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ተደራሽነትን ለማሳደግ ከህብረተሰቡ ጋር በቅንጅት የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

በተጨማሪም የግብርና ትራንስፎርሜሽንን ሊያሳኩ የሚችሉ ግብርናን የማዘመን፤ የቴክኖሎጂ ተጠቃሚነትን የማሳደግ፣ የተሻሻሉ አሰራሮችን የማላመድ፤ የግሉን ዘርፍ የልማት ተሳትፎ በማሳደግ ኢንቨስትመንትን ማጠናከር ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም አስታውቀዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የአርብቶ አደሩን ህይወት በመቀየር የተረጋጋ ኑሮ እንዲኖር የሚያስችሉ የጤና፣ የትምህርት፤  የመስኖ ልማት እና ሌሎች አስፈላጊ መሠረተ ልማቶችን ተደራሽ ለማድረግ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

በውይይቱ የተነሱ የመሰረተ ልማት፤ የመልካም አስተዳደርና እና ተያያዥ ጥያቄዎችን በአጭር ጊዜ፤ በመካከለኛ እንዲሁም በረዥም ጊዜ ዕቅድ ለመመለስ ታቅዶ የሚሰራ ስለመሆኑም አስረድተዋል።  

ወጣቱ የህብረተሰብ ክፍል ቁጭ ብሎ ስራ የሚጠብቅ ሳይሆን በእውቀትና ክህሎት ብቁ ሆኖ በመገኘት ስራን መፍጠር እንደሚገባም ገልጸው፤ መንግስት አስፈላጊውን ድጋፍ እንደሚያደርግ ተናግረዋል።

ሰላምን በተመለከተ ባነሱት ሀሳብ ጥያቄዎች ሲኖሩ በመጠፋፋት ሳይሆን ቁጭ ብሎ በመመካከር እንዲሆን፣ ግጭትን ከሚነግዱ አካላት ራስን በመጠበቅ፣ ህግና ስረዓት በማስከበር፣ የመልካም አስተዳደር ጉዳዮችን በመፍታት በአካባቢው የግጭት ታሪክ እየቀየርን፤ ዘላቂ ሰላምን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በብልፅግና ዘመን መበታተን ቦታ እንደሌለው ጠቅሰው፤ አንድነታችንና ህብረታችንን በመጠበቅ፤ አካባባዊነትንና ከፋፋይነትን በማስወገድ በወንድማማችነት እሴቶች የተገነባ የህዝቦች አንድነትን ማጠናከር እንደሚገባ አሳስበዋል።

የክልሉ መንግስት በጊዜ የለንም መንፈስ ጥያቄዎችን ለመመለስ እንደሚሰራም ገልፀው፤ ህብረተሰቡም ለአመራሩ ጊዜ በመስጠትና የልማቱ አካል በመሆን በትብብር አካባቢውን ለመቀየር መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው ከሁለቱም ዞኖች የተነሱ ሀሳቦች ተገቢ መሆናቸውን በመጥቀስ በተጠናና በተደራጀ ሁኔታ ምላሽ ለመስጠት እንደሚሰራ ገልፀዋል።

አከባቢው ባለዉ ትልቅ ፀጋ ልክ እስካሁን አለመልማቱን የጠቆሙት ኃላፊዉ፤ በቀጣይ ከተለያዩ ባለድርሻ አካላት ጋር በመነጋገር የመንገድ፣ የዉሃ እና ተያያዥ ጥያቄዎችን ለመመለስ የሚሰራ መሆኑን ተናግረዋል።

Leave a Reply