“ክልሉን በሚመጥን መልኩ በስድስቱም የክልሉ ማዕከላት በመገንባት ላይ የሚገኙ የተቋማት ህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በፈጠነ ጊዜ አጠናቆ ለአገልግሎት ለማብቃት የሁሉም አካላት ቅንጅትና ትብብር ያስፈልጋል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ   

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት በክልሉ የወላይታ ሶዶ ማዕከል የክልል ተቋማት የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክት ያለበት ደረጃ የመስክ ጉብኝት፤ የእስካሁን የግንባታ አጻጸም ግምገማ እንዲሁም ይፋዊ የመሠረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ሥነ-ስርዓት በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሃ ግብሩ፤ የክልሉን ህዝቦች ፍትሀዊ ተጠቃሚነት እና አብሮ የመልማት ትልም ዕውን ማድረግ በሚያስችል አግባብ ክልሉ በስድስት ማዕከላት ተደራጅቶ ወደ ስራ በመግባት፤ ባለፉት ሁለት ዓመታት በክልሉ ህዝቡ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በበርካታ ውጤቶች የታጀበ ስኬታማ ጉዞ በማድረግ ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

እንደ ሀገር የኢትዮጵያን የንጋት ዘመን ጅማሮ ያበሰሩ ትውልድ ተሻጋሪ ፕሮጀክቶች በተጠናቀቁበት፤ እንደ ክልልም በርካታ አመርቂ ስኬቶች በተመዘገቡበት በዚህ ታሪካዊ ወቅት፤ የውጤት ዘላቂነትን ለማረጋገጥ በ6ቱም የክላስተር ማዕከላት የተቋማት ህንፃ ግንባታዎች በፍጥነት ተጀምረው ወደ ግንባታ መገባቱን ገልፀዋል፡፡

ከዚህ ቀደም በባዶ ቦታ ያለምንም ዝግጅት የመሰረተ ድንጋይ የማስቀመጥ ባህልን በመሻር ስራው ከተጀመረ በኃላ  መሰረተ ድንጋይ በማስቀመጥ እና ክትትል በማድረግ የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶቹን በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ዓላማን በመሰነቅ በዛሬው ዕለት በስድስቱም ማዕከላት ተመሳሳይ መርሃ ግብሮች በመካሄድ ላይ ስለመሆኑም ተናግረዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በየማዕከላቱ ታቅደው ተገቢውን ሂደት በማለፍ በግንባታ ላይ የሚገኙት የተቋማት ህንፃ ግንባታዎች፤ በክልሉ በላቀ ውጤታማነት የህዝቡን ፍትሀዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለተጀመረው ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ ስኬት ሚናቸው የጎላ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የተቋማት የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶቹ የክልሉን የአስፈጻሚ ተቋማት ተቋማዊ አቅም በማጠናከር፤ በተሻለ የመፈጸምና የማስፈጸም አቅም ለክልላዊ የልማትና የብልጽግና ራዕይ ስኬት አበርክቷቸው ከፍ ያለ መሆኑንም ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግስት ለፕሮጀክቶቹ ልዩ ትኩረት መስጠቱን ተናግረዋል፡፡  

ፕሮጀክቶቹ ከዲዛይን ጀምሮ የክልሉን ሕዝቦች የአንድነትና የወንድማማችነት እሴቶችንና ክልላዊ የሰላም፤ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ራዕይን ታሳቢ ያደረጉ መሆኑን ያወሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ግንባታዎቹ ባጭር ጊዜ ውስጥ በሁሉም የክልሉ ክላስተር ማዕከላት ተጀምረው እየሄዱ ያለበት አግባብ አበረታች መሆኑን ገልፀዋል፡፡ 

የለውጡ መንግስት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ በተያዘላቸው ጊዜ ማጠናቀቅን ባህል ማድረጉንም ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግስት የህንፃ ግንባታዎቹን በጥራትና በፍጥነት ከተያዘላቸው ጊዜ ቀድሞ በማጠናቀቅ የሀብት ብክነትን ለማስቀረትና ምቹ የስራ ከባቢን በመፍጠር የተቋማት አቅም ለማጎልበት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዛሬው ዕለትም በሁሉም ክላስተር ማዕከላት በመካሄድ ላይ የሚገኘው የመስክ ድጋፍና ክትትል የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በሁሉም ማዕከላት ለግንባታዎቹ ይፋዊ የመሠረተ ድንጋይ በማስቀመጥ ጭምር ለህንፃዎቹ በፍጥነት መጠናቀቅ በከፍተኛ ቁርጠኝነትና በላቀ ትኩረት የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ፕሮጀክቶቹ ባጠረ ጊዜ በተሻለ ጥራትና ፍጥነት ግንባታቸው ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆኑ ለማስቻል፤ የባለድርሻ አካላት ቅንጅት እንዲሁም ጠንካራ ድጋፍና ክትትል አስፈላጊ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በቀጣይም በስድስቱም ክላስተር ማዕከላት ያሉ አስተባባሪዎችና የተቋማት የስራ ኃላፊዎች ፕሮጀክቶችን በቅርበት የሚከታተሉበት፤ የሚገመግሙበት እና ለሚገጥሙ ችግሮች መፍትሄ እየሰጡ የሚሄዱበትን አሰራር በመዘርጋት ጭምር ባጠረ ጊዜ በጥራት ገንብቶ ለማጠናቀቅ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የህንፃ ግንባታዎቹ በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም በወላይታ ሶዶ ማዕከል የክልሉን ርዕሰ መስተዳደር ጽህፈት ቤት እና የቤተ-መንግስት ግንባታን ጨምሮ የመስክ ምልከታ ያደረጉ ሲሆን፤ ለህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶቹም በይፋ የመሠረተ ድንጋይ አኑረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የተቋማት የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክት ባጠረ ጊዜ መጠናቀቅ ካለው ዘርፈ ብዙ ጠቀሜታ አኳያ፤ በስድስቱም ክላስተር ማዕከላት የተቋማት ህንፃ ግንባታዎችን በማስጀመር ግንባታቸው በጥራትና በፍጥነት  ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ እንዲሆኑ በትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡  

Leave a Reply