“የህዝብ ጥያቄን ለማዳመጥና አቅም በፈቀደ መጠን ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት የክልሉ መንግስት ከላይ እስከታች  በሩ ክፍት ነው” ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

በክልሉ በጎፋ ዞን ይፋዊ የስራ ቆይታ በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ከዞኑና ከሳውላ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍል ተወካዮች እና አመራሮች ጋር በሰላም፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በመምከር ላይ ይገኛሉ።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድር በውይይቱ ሳውላ ከተማ ሲደርሱ ለተደረገላቸው እጅግ ደማቅ አቀባበል እና መላው የአካባቢው ህብረተሰብ ላሳያቸው ፍቅርና ልባዊ አክብሮት የላቀ ምስጋና አቅርበዋል። 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል የብዝኃነትና የኅብረ-ብሔራዊ አንድነት ማሳያ ብቻ ሳይሆን የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉን ህዝብ የልማትና አዳጊ ፍላጎት በብቃት ለመመለስ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ ለይቶ ወደ ሀብት ለመቀየር መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው አዲሱ አመራር ወደ ስልጣን ከመጣ በኋላ፤ በርካታ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን ለመመለስ ባጭር ጊዜ ውስጥ የ100 ቀን እቅድ በማዘጋጀት ወደ ተግባር መግባቱን ገልፀዋል፡፡

በዞኑም ሆነ በከተማ አስተዳደሩ የኢኮኖሚ አዋጪ ዘርፎች ላይ ትኩረት ያደረጉ ኢንቨስትመንቶች መሳብ፣ ግብርናን ትራንስፎርም ማድረግ፤ በሌማት ትሩፋትና በሌሎች ኢኒሼቲቮች ውጤታማ ትግበራ በቤተሰብ ደረጃ ብልጽግናን ማረጋገጥ ትኩረት የሚያሻው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

በተለይ በግብርናው ዘርፍ የዞኑን እምቅ አቅም በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል፤ በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የታገዘ ግብርናን አቅዶ በመተግበር፤ ዞኑ በቡናና ቅመማ ቅመም እንዲሁም በተለያዩ የኤክስፖርት ሰብሎች ምርታማነት ያለውን እምቅ አቅም ተጠቅሞ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡

ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የወንድማማችነት እሴታችንን ተጠቅመን አንድነታችንን በማጠናከር፤ የክልላችንን የተረጋጋ ማህበረ-ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምህዳር በማጎልበት ህዝባችን ጥያቄዎችን በአግባቡ ማቅረብ የሚችልበት እና የልማት ስራዎች በአግባቡ ተፈፃሚ የሚሆኑበት ስርዓት መገንባት ይገባል ሲሉም አስምረዋል፡፡

የክልሉ መንግስት ከላይ እስከታች የህዝብ ጥያቄን ለማድመጥ እና አቅም በፈቀደ መጠን ተገቢውን ምላሽ ለመስጠት በሩ ክፍት መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አሁን ያለው የህዝብ ተነሳሽነት የተጣለብን እምነት ታላቅ መሆኑን የሚያሳይ ብቻ ሳይሆን ለክልሉ መንግስት ትልቅ አቅም በመሆኑ በመተጋገዝ ክልሉን ከፍ ለማድረግ በጋራ እንስራ ሲሉም ጥሪ አቅርበዋል፡፡

Leave a Reply