ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል አንደኛ አመት ታሪካዊ የምስረታ ክብረ በዓል “ከነሐሴ እስከ ነሐሴ” በሚል መሪ ቃል በወላይታ ሶዶ ከተማ በድምቀት ተከብሯል፡፡
በመድረኩ የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ርዕሰ መስተዳድሩ በጎነትና ይቅር ባይነትን ሰንቀን፤ በፈጣሪ ዕርዳታ ክልሉን መስርተን ዛሬ ለምስጋና በመብቃታችን ፈጣሪን እናመሰግናለን ብለዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልልን ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም ስንመሰርት ጥላቻንና መገፋፋትን ወደ ጎን በመተው፤ በሕብረ-ብሔራዊ ወንድማማችነት ተጋምደን፤ በይቅርታ ተሻግረን፤ በሰላምና በፍቅር መንገድ የምንጓዝ እና መዳረሻችንን ሁለንተናዊ የጋራ ብልፅግና ያደረግን ሕዝቦች መሆናችንን በማስመስከር ነው ብለዋል።
ከፈጣሪ ቀጥሎ ይህን ክልል በሰላም መስርተን በልማት ጎዳና እንዲንጓዝ ከጎናችን ሆኖ እያገዘን ለዚህ ስኬት ያበቃን የክልሉ ህዝብ ከፍ ያለ ምስጋና ይገባዋል ሲሉ ተናግረዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ነሐሴ 13/2015 ዓ.ም የክልሉ መንግስት ሲመሠረት በበርካታ ስጋቶችና ጥርጣሬዎች ታጅቦ እንደነበር በንግግራቸው አስተውሰዋል።
ሆኖም መላዉ የክልሉን ህዝቦች በመያዝ፣ በጎነትን በማንገብ፣ ከትናንት በመማር እንዲሁም ዛሬን የተሻለ ለማድረግ የተደረገው ጉዞ ፈተና የበዛበት ቢሆንም፤ የሽግግር ጊዜ እና የመደበኛ የልማት ስራዎች ዕቅድ አዘጋጅቶ በመተግበር እጅግ ውጤታማ ስራዎች መከናወናቸውን ተናግረዋል።
ያጋጠሙን ፈተናዎች ብርታት ሰጥተዉናል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በርካታ ባህል፣ ታሪክ፣ ወግና ስርዓት ያላቸውን የክልሉ ሕዝቦች አቻችሎ በመምራት ረገድ ከኃይማኖት አባቶችና የሀገር ሽማግሌዎች ጋር ተናቦ በመስራት አፍራሽ ተልዕኮ የያዙ ወገኖች ተግባርና ሴራ እንዲሁም ነጠላ ትርክቶችን ማክሸፍ መቻሉን ገልፀዋል።
በቀጣይም የክልሉ መንግስት ትልቅ ኃላፊነት ያለበት መሆኑን ጠቅሰዉ፤ በእስካሁኑ ሂደት ሁሉም ነገር አልጋ ባልጋ ባይሆንም ከጎናቸው ለነበረው የክልሉ ህዝብ እና ያለልዩነት ለማገልገል ቃለ-መሃላ ፈፅሞ ወደ ስራ ለገባው የክልሉ አመራር ምስጋና አቅርበዋል።
ክልሉ በቱሪዝም፣ በግብርና፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፤ በኢንቨስትመንት እና ሌሎችም ዘርፎች ያሉትን ፀጋዎች ይበልጥ ለይቶ በሙሉ ትኩረት ወደ ስራ መግባት እንደሚገባ ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበው፤ በህዝቦች መካከል ያለዉን አንድነት ይበልጥ ማጠናከር የክልሉ መንግስት ቀዳሚ ተግባር እንደሚሆንም ጠቁመዋል።
የአንድ ዓመት ጉዞችን የበለጠ የምንሰራበትን ወኔ ይዘን የምንሄድበት መሆን አለበት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህ ስኬት ሁሉም እንዲረባረብ ጥሪ አቅርበዋል፡፡
ያለፈዉ አንድ ዓመት ጉዞ ለቀጣይ መስፈንጠሪያ በርካታ ስንቅ የተያዘበት መሆኑን አያይዘው ያስረዱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በትብብርና በዉይይት ጥያቄዎችን በመመለስ እና አንድነታችንን ይበልጥ አፅንተን በጋራ በመረባረብ ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ሁሉም በያለበት የበኩሉን አስተዋፅኦ እንዲያበረክት ጠይቀዋል።
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ ህዝበ ውሳኔ በክልሉ ሕዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ አግኝቶ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ.ም በአርባምንጭ ከተማ በተካሄደ ታሪካዊ የምስረታ ጉባኤ የፌደሬሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ በይፋ መመስረቱ ይታወሳል፡፡