ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 2ኛ ዓመት ምሥረታን በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው ለመላው የክልሉ ሕዝቦች እንኳን ለታሪካዊው የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሁለተኛ ዓመት ምሥረታ አደረሳችሁ፤ አደረሰን ያሉ ሲሆን፤ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-

ነሐሴ 13 ክልላችን የፌደሬሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ የተመሠረተበት ታርካዊ ዕለት!

እንኳን ለደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሁለተኛ የምሥረታ ዓመት አደረሰን! አደረሳችሁ!

ቀዳሚው የብዝኃ ሕዝቦች የጋራ ቤት የሆነው ክልላችን በክልሉ ሕዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ፤ ፍጹም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ የህዝበ ውሳኔ ነሐሴ 13 ቀን 2015 ዓ/ም በተካሄደ ታሪካዊ የምስረታ ጉባኤ የፌደረሽኑ 12ኛው ክልል ሆኖ በይፋ ከተመሠረተ እነሆ ዛሬ ሁለተኛ ዓመቱ ነዉ፡፡    

ሰላም፤ ብዝኃነትና ህብረ-ብሔራዊነት መለያው የሆነው ክልላችን፤ የክልሉን ህዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነትና አብሮ የመልማት ትልም ዕውን ማድረግ በሚያስችል አግባብ በስድስት ማዕከላት ተደራጅቶ ወደ ስራ በመግባት ባለፉት ሁለት ዓመታት ለፈተናዎች ያልተበገረ፤ በታላላቅ ስኬቶች የታጀበ፤ ቃልን በተግባር ያረጋገጠ ስኬታማ ጉዞ ማድረግ ችሏል፡፡

የሀገራዊ ለውጡ ፍሬ የሆነው ክልላችን ለክልሉ ህዝቦች ያደሩ የአደረጃጀት ጥያቄዎች አሳታፊና ዲሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በሕገ-መንግስታዊ ማዕቀፍ ታሪካዊ ምላሽ በመስጠት የክልሉ ህዝብ ከግጭት አዙሪት ወጥቶ ፍቱን ሙሉ በሙሉ ወደ ልማት በማዞር በጋራ የመልማት ትልሙን ዕውን ለማድረግ በህብረት በመትጋት ላይ እንዲገኝ አስችሎታል፡፡  

የክልሉ መንግስት ለክልሉ ህዝቦች የጋራ ህልምና ትልም ስኬት ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ሰንቆ፤ በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች በሁሉም የልማት መስኮች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በተለይ የክልሉ መገለጫ ለሆነው ሰላም ልዩ ትኩረት በመስጠት አሳታፊ በሆነው የለውጡ የፖለቲካ ባህል እየተመራ ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግና የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎችን በማጠናከር ብሎም ነባር ሀገር በቀል የሰላም ግንባታ ተቋማትን በመጠቀም በተሰሩ የተቀናጁ ስራዎች በክልሉ አስተማማኝ የሰላምና የፀጥታ ሁኔታ ማረጋገጥ ተችሏል፡፡ 

በተለያዩ የልማት ኢንሸቲቮች ትግበራም መላው የክልሉን ህዝብ በማስተባበር ምርታማነትን በማሳደግ ተረጂነትን ታሪክ ማድረግ የሚያስችሉ ተጨባጭ ለውጦችን ማስመዝገብ የተቻለ ሲሆን፤ ለአረንጓዴ ልማት ስራዎች ትኩረት በመስጠትም ለአረንጓዴ ኢኮኖሚ ግንባታ ከወዲሁ መሰረት የጣሉ ውጤታማ ስራዎችን መስራት ተችሏል፡፡   

የበርካታ ፀጋዎች ባለቤት የሆነው ክልላችን፤ በህዝባችን ንቁ ተሳትፎ የተሳለጠ የምርታማነት ጉዞ ላይ ከመሆኑም ባሻገር በተመሰረተ ባጭር ጊዜ ውሰጥ የተለያዩ ታላላቅ ሀገራዊ ኩነቶችን በተሳካ ሁኔታ በማዘጋጀት አቅሙን ማሳየት ችሏል፡፡   

በአጠቃላይ ባለፉት ሁለት ዓመታት በገጠርም ሆነ በከተማ ለህዝብ አዳርና አዳጊ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ በመስጠት፤ በለውጡ የተቃኙ ክልላዊና ሀገራዊ የልማትና የብልፅግና ትልሞችን ባጭር ጊዜ ዕውን ለማድረግና የህዝባችንን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችል ስኬታማ ጉዞ ማድረግ ችለናል፡፡

በቀጣይም በጋራ ለሰነቅነው የዘላቂ ሰላምና ሁለንተናዊ ብልፅግና ግብ ስኬት በመደመር ዕሳቤና መንገድ እየተመራን፤ በክልሉ ያሉ ፀጋዎችና የመልማት አቅሞች ተጠቅመን በሰላምና በልማት አርበኛው ህዝባችን ግንባር ቀደም ተሳትፎ የተቀናጀ ርብርብ በማድረግ ለላቀ ውጤት የምንተጋ ይሆናል፡፡

ለዚህም በዘመናት አብሮነት የተዛመዱ፤ የተጋመዱ እና ባህል እሴቶቻቸውን ተወራርሰው የተሠናሠሉት የክልላችን ሕዝቦች የህልውናቸው መሠረት የሆነውን በብዝኃነት ውስጥ ያበበ አንድነታችሁን በወንድማማችነት በማፅናትና  ትብብራችሁን ይበልጥ በማጎልበት እንደተለመደው ከክልሉ መንግስት ጎን በመሆን ክልላችንን የሠላም የመቻቻል እና የብልጽግና ተምሳሌት ለማድረግ እጅ ለእጅ ተያይዘን እንድንሰራ ጥሪዬን አስተላልፋለሁ። 

መጪው ጊዜ የስኬት እንድሆን እመኛለሁ!

ፈጣሪ አገራችንና ህዝቦቿን ይባርክ!

Leave a Reply