
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ገቢዎች ቢሮ የ 2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም እና የ 2019 በጀት ዓመት ዕቅድ የተመለከተ ሴክቶራል ጉባኤ በአርባ ምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል።



ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ፡-በክልሉ 2018 የበጀት ዓመት በብዙ መልኩ የስኬት ዓመት እንደነበር ጠቅሰው፤ በክልሉ ህዝብ ባለቤትነት በሁሉም የልማት አውታሮች በተከናወኑ በርካታ ስራዎች፤ ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ውጤታማ ጉዞን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ አመርቂ ውጤቶች ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡



ከምርጫ ማግስት በሙሉ አቅም ወደ ስራ የገባንበት የ2019 የበጀት ዓመት፤ በተመሳሳይ በሁሉም ዘርፍ የላቀ ውጤት በማስመዝገብ ለህዝባችን ዳግም ቃልን በተግባር የምናረጋግጥበት ሊሆን ይገባል ሲሉም አክለዋል፡፡


በዚህ ረገድ የውስጥ አቅምንና ፀጋን በአግባቡ በመለየት እና ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችንና አዳጊ ፍላጎቶች በብቃት መመለስ መሠረታዊ ብቻ ሳይሆን ከአንድ ጠንካራ መንግስት የሚጠበቅ ቁልፍ ተግባር መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ ክልላዊ የሰላምና የብልጽግና ራዕይን በተሟላ መልኩ ማሳካት የሚቻለው የውስጥ ገቢ አቅምን ማሳደግ እና የክልሉን የኢኮኖሚ አቅም ማጎልበት ሲቻል ብቻ መሆኑንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡



ለዚህም የክልሉ መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የክልሉን ህዝብ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለክልላዊ እና ሀገራዊ የሰላም፤ የዘላቂ ልማትና የሁለንተናዊ ብልጽግና ትልም ስኬት ለገቢ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ መሆኑን ገልፀዋል፡፡


በክልሉ ባለፉት ዓመታት ለገቢው ዘርፍ ውጤታማነት የተለያዩ ሪፎርሞችን በማድረግ፤ የህግ ማዕቀፎችን አዘጋጅቶ በመተግበር እና የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱን ለማዘመን በተደረጉ ጥረቶች በክልሉ የዉስጥ ገቢ የመሰብሰብ አቅም ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት በከፍተኛ ደረጀ ማሳደግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡


በዚህ ረገድ በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 32.4 ቢሊዮን ብር ገቢ በመሰብሰብ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለተመዘገበው ስኬት የተጉ የገቢው ዘርፍ አመራሮች፤ ባለሙያዎች እና ባለድርሻ አካላትን አመስግነዋል፡፡
በ2018 በጀት ዓመት መሰብሰብ የተቻለው ገቢ ከ2017 በጀት ዓመት ሲነፃፀር የ13.1 ቢሊዮን ብር ብልጫ ማሳየቱ፤ ፍትሃዊ ገቢን በአግባቡ ለመሰብሰብ በጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፍ የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ ከተቻለ በክልሉ ገና ያልተነካ ገቢ የማመንጨት አቅም መኖሩን በተጨባጭ የሚያሳይ መሆኑንም አስምረዋል።



ያለፈው ዓመት ስኬት በቀጣይ የገቢ ስራዎችን አጠናክሮ ያልሰበሰብናቸው የገቢ አቅሞች ላይ በማተኮር ባለን ፀጋ እና አቅም ልክ ቢሰራ የተሻለ ገቢ መሰብሰብ እንደሚቻል ያመላከተ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በ2019 በጀት ዓመት ከ48 ነጥብ 2 ቢሊዬን ብር በላይ በመሰብሰብ የህዝብን የልማት ጥያቄ በብቃት ለመመለስ በትኩረት እንደሚሰራ ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት ተግተው በመስራት ፍታሃዊ ገቢን ከእቅድ በላይ በመሰብሰብ ያሳኩ መዋቅሮች የመኖራቸውን ያህል ከእቅድ በታች በመሰብሰብ ዝቅተኛ አፈፃፀም ያስመዘገቡም መኖራቸውን ጠቅሰው፤ በጉባኤው የነበሩ ክፍተቶችን በመለየት ለቀጣይ ማረም እንደሚገባ አስገንዝበዋል።



የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በብቃትና በጥራት በመመለስ ጠንካራ ሀገር፤ ክልል እና የበለፀገ ኅብረተሰብ መፍጠር የሚቻለው፤ የገቢ አማራጮችን በማስፋት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ አሟጦ በመሰበሰብ ብቻ መሆኑንም አስምረው፤ ለተያዘው ግብ ስኬት ከወዲሁ ርብርብ እንዲደረግ አሳስበዋል፡፡
የገቢ ጉዳይ ለአንድ ሴክተር ብቻ ተለይቶ የሚሰጥ ተግባር አለመሆኑንም ጠቅሰው፤ አመራሩ፣ ባለሙያው፤ ማህበራዊ ተቋማት እና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለግብር ዘመኑ የገቢ አሰባሰብ ሥራ ስኬታማነት በጋራ የተቀናጀ ርብርብ ሊያደርጉ እንደሚገባ በአጽንኦት ገልፀዋል።



ፍትሃዊና ተአማኒ ገቢን ሰብስቦ በአግባቡ ልማት ላይ ማዋል ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ በተያዘው ዓመትም 75 በመቶ ወጪን በዉስጥ ገቢ የመሸፈን ዕቅድ ተጠናክሮ የሚሰራበት መሆኑን አረጋግጠዋል።
በክልሉ አስተማማኝ የፋይናንስ ምንጭ ለመፍጠር ገቢን አሟጦ መሰብሰብ እንደሚገባም ጠቅሰው፤ በተለይ በመዋቅሮች መካከል ያለው የእድገት ምጣኔ ተመጣጣኝ እንዲሆን ለማስቻል ፍታሃዊ ገቢን በመሰብሰብ በራስ አቅም የልማት ፕሮጀክቶችን ለመሸፈን መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ለዚህም በክልሉ በሳይንሳዊ መንገድ የተካሄደውን የአቅም ልየታ የጥናት ውጤት ወደ ተግባር በመቀየር እና በገቢ ዙሪያ ኅብረተሰቡ በቂ ግንዛቤ እንዲኖረው በመስራት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሃዊ ገቢን በመሰብሰብ የተለያዩ የልማት ፕሮጀክቶችን ሰርቶ ማጠናቀቅ እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በክልሉ ገቢን ለመሰብሰብ ያሉ አመቺ ሁኔታዎችን በተለይም፡- የተዘረጉ የገቢ አሰባሰብ ህጎች፣ ሀገራዊ ፖሊሲ፣ የህዝብና መንግስት የመደጋገፍ ባህል መጠናከር እንዲሁም የባለድርሻ አካላት ቅንጅትን በአግባቡ መጠቀም እንደሚገባም ርዕሰ መስተዳድሩ አስገንዝበዋል።

የክልሉ ገቢዎች ቢሮ ኃላፊ ወ/ሮ ዓለምነሽ ደመቀ በበኩላቸው፤ ክልሉ በአዲስ መልክ ከተደራጀበት ከ2016 ዓ/ም ጀምሮ የክልሉን የወጪ ፍላጎት 75 በመቶ መሸፈን የሚያስችል ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ ወደ ስራ መገባቱን አስታውሰው፤ ባለፉት 3 ዓመታት በየዓመቱ ከ7.4 ቢሊዮን ብር በላይ የገቢ ዕድገት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በተጠናቀቀው የ2018 በጀት ዓመት 32.4 ቢሊዮን ብር ገቢ ለመሰብሰብ ታቅዶ በተደረገው ርብርብ ዕቅዱን ሙሉ ሙሉ በማሳካት አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ወ/ሮ ዓለምነሽ አስታውቀዋል፡፡
በክልሉ የገቢ ዘርፉን ለማጠናከር ተቋማዊ የመፈጸም አቅም በማሳደግና ብልሹ አሠራርን በማስወገድ የገቢ ስራው በዲጅታል ቴክኖሎጂ በመታገዝ መሠራቱንም ተናግረዋል።
በ2019 የበጀት ዓመት የክልሉን ወጪ 75 በመቶ በውስጥ አቅም ለመሸፈን የታቀደውን ግብ ለማሳካት በቅንጅት የሚሠራ መሆኑንም የቢሮ ሃላፊዋ አመልክተዋል።



በመድረኩ ማጠቃለያ በክልሉ በ2018 በጀት ዓመት በገቢ ስራዎች የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ መዋቅሮች እና ባለሙያዎች በክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ እውቅናና ሽልማት ተሰጥቷቸዋል፡፡






በዚህም ከዞኖች፡- ጋሞ ዞን እና አሪ ዞን በ1ኛ ደረጃ፤ የደቡብ ኦሞ ዞን እና ወላይታ ዞን በ2ኛ ደረጃ እንዲሁም የኮንሶ ዞን እና የጌዴኦ ዞን በ3ኛ ደረጃ ተሸላሚ ሆነዋል።
በተጨማሪም በክልሉ ከሚገኙ 3ቱ የሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች መካከል ዲላ ከተማ በአንደኝነት ተሸላሚ ሆኗል።





