
በትላንትናው ዕለት የተካሄደዉ ታሪካዊው የ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እጅግ ሰላማዊ በሆነ መንገድ ዴሞክራሲያዊ ሂደቱን ጠብቆ በስኬት በመጠናቀቁ የተሰማኝን ልባዊ ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ፡፡
መላው የክልላችን ሕዝቦች በቅድመ ምርጫው፣ በምርጫው እንዲሁም በድህረ ምርጫ ወቅት ለሀገራችን መፃይ ብሩህ ተስፋ ቀናኢ በመሆን ባሳያችሁትና እያሳያችሁት ባላችሁት ትጋት እና ፅናት የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ጉዟችንን በማፅናት ዳግም አሸናፊ እንድንሆን አስችሎናል።
በዚህ አጋጣሚ በምርጫው የተፎካከሩ የፖለቲካ ፓርቲዎችም ሆኑ እጩዎች፤ ሕዝባችን በነፃነት የሰጠውን ድምፅ በፀጋ በመቀበል እና በምርጫው የገለጸውን ፍላጎት በማክበር በጋራ ተባብረን ሀገር ለማሻገር ትልቅ አደራ መቀበላችንን ሊንገነዘብ ይገባል፡፡
በክልላችን እንደ ሀገር ለምናልመው የዴሞክራሲ ስርዓት ግንባታ ዕውን መሆን በምርጫው በነቂስ በመሳተፍ ድምጻችሁን የሰጣችሁ ዜጎች እንዲሁም በምርጫው የተሳተፋችሁ የተፎካካሪ ፓርቲዎች እና የግል ተወዳዳሪዎች፤ የምርጫው ሂደት ሰላማዊ፤ ነፃና ዴሞክራሲያዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ የበኩላችሁን ሚና በመወጣት ላበረከታችሁት ጉልህ አስትዋጽኦ በክልሉ ህዝብና መንግስት ስም ልባዊ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ፡፡
እንደዚሁም የምርጫ አስፈጻሚዎች፤ ታዛቢዎች፤ የሲቪክ ማህበራት እና ሚዲያዎች እንዲሁም የፀጥታና ደህንነት አካላት የምርጫው የድምጽ አሰጣጥ ሂደት እጅግ ሰላማዊ፤ ነፃና ፍትሃዊ በሆነ ሁኔታ በስኬት እንዲጠናቀቅ ላበረከታችሁት የላቀ አስትዋጽኦ ልባዊ ምስጋናዬ ይድረሳችሁ፡፡
በመጨረሻም በቅድመ ምርጫው እና በምርጫው ሂደት እንደታየው ስክነትና ህዝባዊ አንድነት፤ የድህረ ምርጫው ሂደትም እጅግ በሰከነ፤ በሰለጠነና ሰላማዊ በሆነ ሁኔታ ከፍጻሜው እንዲደርስ በማስቻል፤ በልማትና በመልካም አስተዳደር ስራዎች በጋራ በመረባረብ የህዝባችንን ተጠቃሚነት እዉን ለማድረግ ሁላችንም የድርሻችንን እንዲንወጣ ጥሪዬን ለማስተላለፍ እወዳለሁ።
ፈጣሪ ኢትዮጵያና ህዝቦቿን ይባርክ!
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር





