“ብልፅግና የሀገር ከፍታንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን አስቀድሞ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር በመትጋት ላይ ይገኛል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ  

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን በማስመልከት የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ዞናዊ ማጠቃለያ እና ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በክልሉ በጋሞ ዞን፤ በአርባ ምንጭ ከተማ በታላቅ ህዝባዊ ተሳትፎ ተካሂዷል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመርሃ ግብሩ ባስተላለፉት መልዕክት፡- 7ተኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ እንደ ሀገር ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በማጎልበት ሀገርንም ሆነ ክልላችንን ወደ ተምሳሌት ለማሸጋገር በመደረግ ላይ ላለው ጥረት ስኬት ቁልፍ በመሆኑ ምርጫው ሰላማዊ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቅርበዋል።

ብልጽግና የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተግባር በማረጋገጥ ክልላችንንም ሆነ የጋሞ ዞንና አርባ ምንጭ ከተማን እንዲበለፅጉ እየተጋ ያለ ፓርቲ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መላዉ የዞኑ እና የከተማው ነዋሪ ግንቦት 24 በሚካሄደው ምርጫ ብልፅግናን በመምረጥ ከፓርቲው ጋር ያላቸውን ቃል ኪዳን እንዲያድሱ ጠይቀዋል።

ፓርቲው ባለፉት የለውጥ ዓመታት ሀገራችን ገጥመዋት ከነበረው የመፍረስና የበተን አደጋ በማውጣት እና ፈተናዎችን በጽናት ወደ ዕድል በመቀየር ባከናወናቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ስራዎች በከተማም ሆነ በገጠር ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍል ተጠቃሚ ያደረጉ ስኬቶችን ማስመዝገቡን ተናግረዋል፡፡

በተለይ የተረጂነትና የጠባቂነት እሳቤን በመስበር እንዲሁም ሀገራዊ አቅሞችን ለይቶ መጠቀም ያስቻሉ የፖሊሲ ማሻሻያዎችንና በርካታ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመተግበር የማይቻል በሚመስሉ መስኮች ጭምር ምርታማነትን በማሳደግ የታሪክ ዕጥፋት ማስመዝገብ መቻሉን ገልፀዋል፡፡

ብልፅግና ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባህልን በማጎልበት ያጠናቀቃቸው ዘርፈ ብዙ የልማት ፕሮጀክቶች እና ተግባራዊ ያደረጋቸው ሰው ተኮር የልማት ተግባራት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ስኬታማ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ፓርቲው ለህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ከመስጠት ባሻገር በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በመግለጥ በገጠርም ሆነ በከተሞች ልማት ባስመዘገባቸው ተጨባጭ ስኬቶች በተጨበጠ ውጤት የወደፊት ብሩህ ተስፋን አሻግሮ ማየት ያስቻለ ስለመሆኑም በአጽንኦት ገልፀዋል።

ብልፅግና የተሻለ ነገን በማለም የሀገር ከፍታንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን አስቀድሞ በተደማሪ አቅም ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር በመትጋት ላይ የሚገኝ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ፓርቲው የሀገርን ኢኮኖሚያዊ፣ ማህበራዊና የቴክኖሎጂ እድገት ትጋቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አስታውቀዋል።

በክልሉ እንዲሁም በጋሞ ዞን እና በአርባምንጭ ከተማ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የልማት ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ እንዲሁም አርባ ምንጭን የቱሪዝምና የኮንፈረንስ ማዕከል ለማድረግ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር የብልፅግና ጉዞን ለማፅናት ህዝቡ ግንቦት 24 በነቂስ ወጥቶ ድምጹን ለብልፅግና በመስጠት ዳግም አጋርነቱን እንዲያረጋግጥም ጥሪ አቅርበዋል።

የጋሞ ዞን ዋና አስተዳዳሪ ደምስ አድማሱ (ዶ/ር)  በበኩላቸው፤ ብልፅግና ፓርቲ የሀገራችንን ሁለንተናዊ ብልፅግና በማረጋገጥ በአፍሪካ ተምሳሌት ሀገር እንድትሆን እየተጋ ይገኛል ብለዋል።

በዞኑ የተጀመሩ ሁለንተናዊ የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ተግባራት ተጠናክረው እንዲቀጥሉ መላዉ የዞኑ ነዋሪ ግንቦት 24/2018 ዓ.ም በሚደረገው ሀገራዊ ምርጫ በነቂስ በመሳተፍ ብልፅግና ፓርቲን እንዲመርጥም ጥሪ አቅርበዋል።

የአርባ ምንጭ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ መስፍን መንዛ (ዶ/ር) የእንኳን ደህና መጣችሁ መልዕክት ባስተላለፉበት ወቅት፤ ሀገራዊ ለውጡን ተከትሎ መንግስት ለህዝብ ከገባው ቃል አንዱና ዋነኛው የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ላይ ይስተዋል የነበረውን ስብራት መጠገን ሲሆን፤  ይህን የሚያረጋግጡ ዘርፈ ብዙ ተግባራት ተከናውነዋል ብለዋል።

ባለፉት የለውጥ አመታት በከተማው የተከናወኑ የመሠረተ ልማት ተግባራት የከተማዋን ገፅታ ከመቀየር ባሻገር ለነዋሪዎች ምቹ እንድትሆን አድርጓታል ያሉት ከንቲባው፤ በከተማው የተጀመረውን ሁለንተናዊ የለውጥ ጉዞ ለማስቀጠል መላው የከተማው ነዋሪ የብልፅግና ፓርቲን እንዲመርጥም ጥሪ አቅርበዋል።

Leave a Reply