“የስንዴ ነዶን በመምረጥ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር የተጀመሩ ሁለንተናዊ ልማቶች ማስቀጠል ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ በማስመልከት የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና ጋሞ ዞንን ወክለው ለህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እና ለክልል ምክር ቤት የሚወዳደሩ ዕጩዎችን የሚያስተዋውቅ የድጋፍ ሰልፍ በአርባ ምንጭ ከተማ በድምቀት ተካሂዷል፡፡

በመርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፡- ብልጽግና ፓርቲ ባለፉት የለውጥ አመታት በፖለቲካ ባህላችን ላይ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፣ በታላላቅ ስኬቶች የታጀበ፣ ቃልን በተግባር ያረጋገጠ ስኬታማ ጉዞ ማድረግ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በጠራ ራዕይ እየተመራ፤ ሉዓላዊነቷ በሙላት የተከበረ፤ ሁለንተናዊ ብልጽግናዋ የተረጋገጠ ተምሳሌታዊ ሀገር ለትውልድ የማሻገር ራዕይ በመሰነቅ፤ በማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ዘርፎች ባስመዘገባቸው አስደናቂ ስኬቶች ኢትዮጵያን አጓጊ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንዲትገኝ ማስቻሉንም ገልፀዋል፡፡

በተለይ ለህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎች ደረጃ በደረጃ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ የጠባቂነትና የተረጂነት እሳቤን በመስበር እና በሀገር በቀል እሳቤዎች ሀገራዊ አቅሞችን በመጠቀም በሁሉም የልማት አውታሮች ባስመዘገባቸው ተጨባጭ ውጤቶች አይቀረ የሆነው የኢትዮጵያን ብልጽግና በማይቀለበስ መሠረት ላይ ማስቀመጥ መቻሉንም አስገንዝበዋል፡፡

ፓርቲው ተግባራዊ ያደረጋቸው ሰው ተኮር የልማት ስራዎች ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ከማድረግ አኳያ ስኬታማ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ብልፅግና ፓርቲ ትላንትም ስራ ላይ የነበረ፤ ዛሬም የሀገር ከፍታንና የሕዝብ ተጠቃሚነትን አስቀድሞ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር በመትጋት ላይ የሚገኝ መሆኑንም በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡

የተሻለች ሀገር ለትውልድ ለማሻገር የጀመርነው ጉዞ ሊቀጥል የሚችለው የደጋፊዎቻችን እና የመላው ሕዝባችን ጥረት ሲታከልበት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በምርጫ ሰበብ የግል ጥቅማቸውን ለማስከበር ከሚመጡ አደናጋሪዎች ህዝቡ ራሱን ሊጠብቅ እንደሚገባው አስገንዝበዋል።

መላው የክልሉ ሕዝብ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፣ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በምርጫው ሂደት የበኩሉን እንዲወጣም ጥሪ አቅርበዋል፡፡ መልዕክት አስተላልፈዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም የስንዴ ነዶን በመምረጥ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር የተጀመሩ፤ የሕዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ ሁለንተናዊ ልማቶች እናስቀጥል ሲሉ መልዕክት በማስተላለፍ ንግግራቸውን አጠቃለዋል።

በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፤ ነፃ፤ ፍትሃዊ እና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ በሁሉም ረገድ በቂ ዝግጅት የተደረገ ሲሆን፤ በምርጫው የምሳተፉ ፓርቲዎች በህግ በተፈቀደው አግባብ ፕሮግራሞቻቸውን እና ዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸውን ለሕዝብ በማስተዋወቅ ላይ ይገኛሉ፡፡

በክልሉ ብልፅግና ፓርቲ በተመሳሳይ የምርጫ ቅስቀሳውን በክልሉ በሚገኙ በሁሉም የምርጫ ክልሎች በሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎ ማካሄዱን አጠናክሮ የቀጠለ ሲሆን፤ በመርሃ ግብሮቹ ፓርቲው በየምርጫ ክልሉ ያቀረባቸውን ዕጩ ተወዳዳሪዎች ከማስተዋወቅ ባለፈ፤ ኢትዮጵያን ወደ ተምሳሌት ሀገር ለማሻገር ለሰነቀው ራዕይ የነደፋቸውን ፕሮግራሞች በሰፊው በማስተዋወቅ ላይ የሚገኝ መሆኑም ተመልክቷል፡፡

Leave a Reply