“መንግስት መሰረታዊ የሆነውን ፍትሃዊ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን ለማሳደግ በቁርጠኝነት በመስራት ላይ ይገኛል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በወላይታ ዞን ሆቢቻ ወረዳ የተገነባ የንፁሁ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት በይፋ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡

ንፁህ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክቱ ከ150 ሚሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ የክልሉ መንግስት ከፌዴራል የውሃና ኢነርጂ ሚንስትር እና ከዞኑ አስተዳደር ጋር በመተባበር ያስገነባው ሲሆን፤ ከ31 ሺህ በላይ ለሚሆኑ ዜጎች አገልግሎት መስጠት የሚችል መሆኑም ታውቋል።

በመርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የሆቢቻ ወረዳ የብዝሃ ቀበሌ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት የአካባቢውን ነዋሪዎች የዘመናት የንፁሁ የመጠጥ ውሃ ጥያቄ ምላሽ መስጠት የቻለ መሆኑን ጠቅሰው፤ ፕሮጀክቱ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ በመሆኑ የተሰማቸውን ደስታ ገልፀዋል፡፡

የፕሮጀክቱ በፍጥነት ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆን፤  የመንግስታችንን ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባህል በማዳበር የህብረተሰብ ተጠቃሚነት በማረጋገጡ ረገድ፤ ቃልን በተግባር በመቀየር ላይ መሆኑን ማሳያ ነው ሲሉም አክለዋል።

የክልሉ መንግስት መሠረታዊ የሆነውን ፍትሃዊ የንፁህ መጠጥ ውሃ ተደራሽነትን በማሳደግ የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከፌዴራል መንግስት፤ በየደረጃው ካሉ መዋቅሮች እና ሌሎች አጋር ተቋማት ጋር በትኩረት በመስራት ላይ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በዛሬው ዕለት የተመረቀው የንፁህ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክት የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ ባለፉ ጊዜያቶች በተሰሩ በርካታ ስራዎች የንፁህ መጠጥ ውሃ ሽፋንን በእጅጉ ማሳደግ መቻሉንና ይህም ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

የክልሉ መንግስት የህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቁዎችን ደረጃ በደረጃ ምላሽ ከመስጠት ባለፈ ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ባጠረ ጊዜ ዕውን ለማድረግ መላው የክልሉን ህዝብ አስተባብሮ በሙሉ አቅሙ በመስራት ላይ መሆኑንም አያይዘው ገልፀዋል፡፡

ሰላማችንን ጠብቀን በሁሉም የልማት መስኮች እጅ ለእጅ ተያይዘን በኅብረትና በአንድነት ፀጋዎቻችንን በመግለጥ ተባብረን ከሰራን የምንሻውን ዕድገትና ልማት በአጭር ጊዜ ዕውን ማድረግ እንችላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህብረተሰቡ ሰላምን በማፅናት ከክልሉ መንግስት ጎን ተሰልፎ የልማት ትብብሮችን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

የተመረቀው የውሃ ፕሮጀክት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ በአካባቢው ለሁለንተናዊ የዘላቂ ልማት በመደረግ ላይ ላለው ጥረት ትልቅ አቅም የሚፈጥር መሆኑንም ገልፀዋል።

ውሃ ህይወት ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በከፍተኛ ወጪ የተገነባውን የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክት፤ ጠብቆ ተንከባክቦ በማቆየት ህብረተሰቡን በአግባቡ ማገልገል እንዲችል መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የተገነባው የንፁሁ የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቱ በአግባቡ ከተያዘ ለቀጣይ 15 ዓመታት ህብረተሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ እዲችል ታስቦ የተገነባ መሆኑንም አስታውቀዋል።

በዘላቂነት ውሃ ለማግኝት የተፈጥሮ ሀብት ልማት ጥበቃ ስራዎችን አጠናክሮ ተፈጥሮን መንከባከብ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የአካባቢው ህብረተሰብ አረንጓዴ አሻራን ባህል በማድረግ ዛፍ የመትከልና ተፈጥሮን የመንከባከብ ስራዎችን በዘላቂነት እንዲያከናውን ከአደራ ጭምር አሳስበዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ለኢፌድሪ ውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር እና ሌሎች ለፕሮጀክቱ ስኬት የድርሻቸውን ላበረከቱ አካላት በክልሉ መንግስትና ህዝብ ስም ላቅ ያለ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የውሃና ኢነርጂ ሚንስቴር ዴኤታ አቶ አስፋው ዲንጋሞ በበኩላቸው፤ ፍትሃዊ የንፁህ ውሃ ተጠቃሚነትንና ተደራሽነትን ለማስፋት የውሃ ተቋማት የማስተዳደር አቅም ማሳደግ አስፈላጊ መሆኑን ገልፀው፤ በዚህ ረገድ በሚወጣው ታሪፍ መሰረት የአገልገሎት ክፍያ  በአግባቡ መክፈል እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

የክልሉ ውሃና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ ኢ/ር አክልሉ አዳኝ በበኩላቸው፤ ቢሮው በየደረጃው ካሉ አጋር አካላት ጋር በመሆን በክልሉ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ለማሳደግና ተደራሽ ለማድረግ የሚያስችሉ ስራዎችን በመስራት ላይ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ በዛሬው ዕለት የተመረቀው የሆቢቻ ወረዳ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትም የዚሁ ጥረትና ትብብር አካል መሆኑን ገልፀዋል።

የክልሉ መንግስት ለማህበራዊ ብልፅግና ትልም ስኬት የመሠረታዊ አገልገሎቶች ተደራሽነትን ለማሳደግ በትኩረት በመስራት ላይ ሲሆን፤ በተለይ ከመሠረታዊ ፍላጎቶች እጅግ አስፈላጊ የሆነው ፍትሀዊ የንፁሁ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ተደራሽነትን በማስፋት የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት በመስራት ላይ ይገኛል፡፡ 

ለዚሁም ግብ ስኬት ከፌዴራል መንግስት፤ መንግስታዊ ካልሆኑ አጋር ድርጅቶች እና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር በቅርበት በመስራት ላይ ሲሆን፤ በክልሉ የንፁሁ የመጠጥ ውሃ ሽፋን ተደራሽነትን በማሳደጉ ረገድ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ችሏል፡፡

በዚህ ረገድ በተለይ ባለፉት ሁለት ዓመታት ከ3.2 ቢሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ ከ1.2 ሚሊዮን በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የተለያዩ የንፁሁ መጠጥ ወሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን በማስጀመር፤ በለውጡ መንግስት ፕሮጀክቶችን ጀምሮ የመጨረስ ባህል በርካታ ፕሮጀክቶች ተመርቀው አገልግሎት በመስጠት ላይ እንዲገኙ አስችሏል፡፡

በክልሉ በዘንድሮ የ2018 በጀት ዓመት ያለፉ አሥር ወራት ብቻ በከተማና በገጠር 65 የውሃ ፕሮጀክቶችን በማጠናቀቅ ከ421 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉም ታውቋል፡፡

ከዚህ በተጨማሪ በዛሬው ዕለት የተመረቀው የሆቢቻ ወረዳ የንፁሁ የመጠጥ ውሃ ፕሮጀክትን ጨምሮ ከ180 ሺህ በላይ ዜጎችን ተጠቃሚ የሚያደርጉ የአምስት ከተሞች የመጠጥ ውሃና ሳኒቴሽን ፕሮጀክቶችን ከ1.2 ቢሊየን ብር በላይ በሆነ ወጪ ግንባታቸውን በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ በመደረግ ላይ መሆኑንም ማወቅ ተችሏል፡፡

በተጨማሪም ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት በወላይታ ዞን ሆብቻ ወረዳ “በአንድ ወረዳ አንድ የማህበረሰብ ፋርማሲ” ኢኒሼቲቭ አካል የሆነው የማህበረሰብ መድሃኒት መደበር እና እድሳቱ ተጠናቆ በአዲስ መልክ የህክምና ቁሳቁስ የተሟላለት የእናቶች ቀዶ ጥገና ማዕከል ተመርቆ በይፋ አግልግሎት መስጠት ጀምሯል።

Leave a Reply