“ምርጫው ሰላማዊ እና ታአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ የፀጥታ አካላት የፀጥታ ስራዎችን በተጀመረው አግባብ በልዩ ትኩረት ሊሰሩ ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ    

የክልሉ የፀጥታ ምክር ቤት 4ኛ መደበኛ ጉባኤ፤ በክልሉ ባለፉ ዘጠኝ ወራት የተከናወኑ የፀጥታ ስራዎችን በመገምገም እንዲሁም 7ኛው ሀገራዊ ምርጫን ያለምንም የፀጥታ ችግር ነፃ፤ ሰላማዊ፤ ዲሞክራሲያዊና ታአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ በሚያስችሉ የፀጥታ ስራዎች ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ ተጠናቋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመድረኩ የክልሉ መንግስት ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ በመሰነቅ ሰላምና ደህንነቱ የተረጋገጠ፤ በፖለቲካው የሰከነና የተረጋጋ እንዲሁም በራስ አቅም ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ በኢኮኖሚው የበለፀገ ክልል ለመገንባት ዘርፈ ብዙ ውጤታማ ስራዎች በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

ክልሉ በተለይ ሰላምን ቀዳሚው አጀንዳ በማድረግ በርካታ የሰላምና ፀጥታ ስራዎች ሲሰራ መቆየቱን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነት ተግባራትን በማጠናከር እና በመዋቅሮች መካከል ትብበርና ጠንካራ ቅንጅታዊ አሰራርን በማጎልበት በተከናወኑ በርካታ ስራዎች አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉንም ገልፀዋል፡፡

መንግስት ለዘላቂ ሰላምና ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ባለው ቁርጠኝነት በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ባህል በመገንባት በክልሉ ከሚንቀሳቁ ተፎካካሪ የፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በጋራ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ የትብብር ማዕቀፎችን በማጠናከር መስራቱም ለተመዘገበው ውጤት አስትዋጽኦው የጎላ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

እንደ ሀገር ለምንሻው ዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ግንቦት 24 የሚካሄደው 7ኛው ሀገራዊ ምርጫ ፍጹም ሰላማዊ፤ ነፃ፤ ፍትሀዊና ተአማኒ ሆኖ እንዲጠናቀቅ ማስቻል ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህ ረገድ የፀጥታ መዋቅሩ ከፍተኛ ኃላፊነት ያለው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

የቅድመ ምርጫ ስራ አካል በሆነው የመራጮች ምዝገባ በክልሉ ባሉ 56 የምርጫ ክልሎች እና በሁሉም የምርጫ ጣቢያዎች በስኬት መጠናቀቁንም አስታውሰው፤ ለዚህ የፀጥታ አካላት አስትዋፅኦ የጎላ መሆኑን በመጥቀስ በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም ምርጫው በሰላም ተጀምሮ በስኬት እንዲጠናቀቅ በተጀመረው አግባብ የሚሰሩ የቅድመ የምርጫ፣ የምርጫ እና የድህረ ምርጫ ስራዎች እቅድን ከነባራዊ ሁኔታዎች አንጻር በመገምገና በመከለስ በልዩ ትኩረት ተግባራትን ቆጥሮ በማከናወን በስኬት ለማጠናቀቅ መስራት እንደሚገባም አሳስበዋል።

በክልሉ በሁሉም ምርጫ ክልል 7ኛው ሀገራዊ ምርጫን ለማከናወን የሚያስችል አስተማማኝ አስቻይ ሁኔታ መኖሩ መገምገሙን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የፀጥታና ደህንነት ስራዎችን ህብረተሰቡን ባለቤት ባደረገ መልኩ በማጠናከር ይህንኑ አስተማማኝ የፀጥታ ሁኔታ ማስቀጠል እንደሚገባ በአፅኖት ተናግረዋል።

በክልሉ ህገ-መንግስታዊ ስርዓቱን ተከትለው በሰላማዊ መንገድ ምርጫ ከሚወዳድሩ ተፎካካሪ ፓርቲዎች በተጓዳኝ በፖለቲካ ሽፋን ኃይማኖትንና ብሄርን መሰረት ያደረጉ ግጭቶችን ለመቀስቀስ የሚንቀሳቀሱ እና በህገ ወጥ ተግባራት የሚሳተፉ ፓርቲዎች መኖራቸውንም በመጥቀስ የፀጥታ ስራው ከመቸውም ጊዜ በላይ የሁሉንም ቅንጅት የሚሻ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡ 

በመሆኑን በሁሉም መዋቅሮች አመራሩ እና የፀጥታ አካላት ይበልጥ ተቀራርቦና ተቀናጅቶ በመስራት፤ የሚያጋጥሙ ችግሮችን በትዕግስት በመፍታት እና በስነልቦና የበላይነት በመምራት መስራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል።

የፀጥታ አካላት በቀሪ ጊዜያት የክልሉን አስተማማኝ ፀጥታና ደህንነት የሚያረጋግጡ ስራዎችን ከመስራት ባለፈ ከወዲሁ ለ2019 እቅድ መነሻ ሊሆን የሚችል እቅድ በማዘጋጀት በተደራጀ መልኩ ሊሰሩ እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም እንደ ሀገር ለሰነቅነው ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ብቻ ሳይሆን ሁለንተናዊ ብልፅግናዋ ለተረጋገጠ ለጠንካራ ተምሳሌታዊ ሀገር ግንባታ የምርጫው ሰላማዊና ዲሞክራሲያዊ ሆኖ መጠናቀቅ ቁልፍ በመሆኑ የፀጥታ መዋቅሩ የፀጥታ ተግባራትን በብቃት እንዲያከናውን በማሳሰብ ጉባኤውን አጠቃለዋል፡፡

Leave a Reply