
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ ባለፉት ሁለት ቀናት ቀዳሚ የብዝኃ ሕዝቦች የጋራ ቤት በሆነው የሰላም፤ የመቻቻልና የብዝኃነት ተምሳሌቱ ክልላችን ያደረጉት የማይረሳ የስራ ቆይታ ለቀጣይ ስኬታማ ጉዟችን አንድምታው ብዙ ነው፡፡



ከዚህም በላይ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ እና ቀዳማይት እመቤት ዝናሽ ታያቸው በክልላችን በነበራቸው በዚሁ ቆይታ፤ በየደረሱበት የክልላችንን ሕዝቦች አሻጋሪ የሰላም፣ የፍቅር፤ የእንግዳ ተቀባይነት እሴቶችና ቱባ ባህሎች ባንጸባረቀ መልኩ ህዝቡ ያሳየው ከልብ የመነጨ ልባዊ ፍቅርና አክብሮት የመሪያችንን ታላቅነት እና የህዝባችንን ትልቅነት የመሰከረ ነው፡፡



ተፈጥሮ ከኳላት አርባ ምንጭ እስከ ዳሞቷ ፀዳል ውብቷ ወላይታ ሶዶ በዘለቀው ይሄው የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ጉብኝት፤ በየአካባቢው የሚገኘው ህዝባችን በአስደናቂ ኅብር ባህሎቹና እሴቶቹ ታጅቦ፤ በማንነት መገለጫ ቀለሞቹ አሸብርቆ በፍጹም ጨዋነት ክብር ለሚገባው መሪያችን የቸረው ልባዊ ፍቅርና አክብሮት ከልብ የታተመ ብቻ ሳይሆን ለክልላችንም ከፍ ያለ ክብርና ሞገሰ ያጎናፀፈ ነው፡፡






ህዝባችን ለክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያሳየው ልብ የሚሞላ ፍቅርና አክብሮትም እንዲያው የተቸረ ሳይሆን፤ በርግጥም ክብርና ፍቅር የሚገባቸው ታላቅ የሀገር መሪና የክልላችን ህዝቦች የልብ ወዳጅ መሆናቸውን በመገንዘብ ጭምር መሆኑን ማሳብ ያሻል፡፡



ሀገር ዓርብ ላይ ቆማ ዘመናት ሲንከባለሉ በመጡ ውስብስብ ችግሮች ትብታብ የህልውና አደጋን በተጋረጠችበት ፈታኝ የታሪክ ምዕራፍ፤ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ በአስደናቂ ፅናትና ጥበብ፤ በመደመር እሳቤና በጠንካራ የለውጥ አመራር ኢትዮጵያን ከገባችበት ውጥንቅጥ ማሻገር የቻሉ ታላቅ መሪ ናቸው፡፡



ህዝባችን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያና ሕዝቦቿን ከመጠፋፋት ፅልመት በታደገ አመራራቸው ሳይገደቡ፤ ለእኛ ኢትዮጵያዊያን በተለየ የማይቻል ይመስል በረዥሙ የሀገረ መንግስት ታሪካችን እንደ ሀገር መሰነቅ ያቃተንን የብልፅግና ራዕይ ሰንቀው የመላ ኢትዮጵያዊያን የጋራ ህልምና ትልም ማድረግ የቻሉ ድንቅ መሪ መሆናቸውንም ይረዳል፡፡



የሀገራዊ ለውጡ መሐንዲስ የሆኑት ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ በሚጋጩ ህልሞቻቸው ተሳክረው ሀገር ለማፍረስ የሚተጉን ይቅርታና ፍቅርን አስቀድመው መስመር ከማስያዝ ባለፈ በህዝቡ ባለቤትነት በርካታ የታሪክና የባህል ዕጥፋት በማስመዝገብ የኢትዮጵን ብልፅግና ለማዋለድ መሰረት የጣሉ ስኬቶች እንዲመዘገቡ ያስቻሉም ናቸው፡፡



በክልላችን ሕዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ ከተመሠረተ ድፍን ሁለት ዓመት ሊሞላው በጣት የሚቆጠሩ ቀናት የቀሩት የለውጡ ፍሬ የሆነው የክልላችን ምስረታም፤ ያለ ክቡር ጠቅላይ ሚኒስትራችን ቆራጥ አመራርና ድጋፍ የማይታሰብ መሆኑን ህዝባችን በውል ይገነዘባል፡፡



የክልሉ መንግስት ለክልሉ ህዝቦች የጋራ ህልምና ትልም ስኬት ክልላዊ የሰላምና የብልፅግና ራዕይ ሰንቆ ባለፉት 2 ዓመታት በክልሉ የተረጋጋ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ምኅዳር በመፍጠር በሁሉም የልማት አውታሮች አመርቂ ውጤት በማስመዝገብ በቀጠለው ስኬታማ ጉዞ የክቡር ጠቅላይ ሚኒስትሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ አስትዋጽኦው የጎላ ነው፡፡
ያለፉት ሁለት ቀናት ጉብኝታቸውም በክልላችን መነቃቃት የፈጠረ፤ ለቀጣይ ስኬታማ ጉዟችን ተጨማሪ አቅምና ጉልበት የገነባም ነው፡፡






ክብር ጠቅላይ ሚኒስትራችን የክልላችን ህዝቦች ወዳጅ ብቻ ሳይሆኑ የሀገር ባለውለታ ጭምር ስለመሆናቸው በነበራቸው በዚሁ ቆይታ፤ ህዝባችን ከአርባ ምንጭ ጎዳናዎች እስከ ለምለምቱ ወላይታ በህዝብ ማዕበል በታጀበ ልብ የሚያሞቅ አቀባበል ከልብ የታተመ ልባዊ ፍቅሩንና አክብሮቱን በመግለጽ አሳይቷቸዋል፡፡

አክብሮትና ፍቅር የምገባው መሪያችንን አክብራችሁ ሞገስ ለሆናችሁን የክልላችን ሕዝቦች ሁሉ ልባዊ ምስጋናችን ይደረሳችሁ!!
#ርዕሰመስተዳድርጽቤት