
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ከክረምት የወጣቶች የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ጋር በተያያዘ ባስተላለፉት መልዕክት ወጣቱ የነገ ሀገር ተረካቢ ብቻ ሳይሆን ዛሬም በንቁ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ተሳትፎ አካባቢውንና ሀገሩን ለመለወጥ የድርሻውን የሚወጣ፤ ለማህበረሰቡ አወንታዊ ለውጥ የሚተጋ ግንባር ቀደም የልማት ኃይል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
ለዚህ ባለፉ የለውጥ አመታት እንደ ሀገር በለውጡ መንግስት መሪነት እና በህብረተሰቡ ተሳትፎ እየተከናወነ በሚገኘው የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት በወጣቱ ንቁ ተሳትፎ ማስመዝገብ የተቻለው አመርቂ ውጤት ማሳያ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ከጊዜ ወደ ጊዜ እያደገና እየሰፋ የመጣው የወጣቱ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎና በየአካባቢው የሚታዩ ሰው ተኮር ተግባራት፤ ለሀገራችን ዘላቂ ሰላምና ልማት ብሎም ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ አበርክቶው የጎላ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በክልሉ በተመሳሳይ እያደገ የመጣው የወጣቶች የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተሳትፎ እና በህብረተሰቡ ዘንድ እየታየ ያለው ተነሳሽነት የሚበረታታ፤ ተስፋ ሰጪና ባህል ሆኖ ሊቀጥል የሚገባው ታላቅ ሰው ተኮር ተግባር ነው ሲሉ አስምረውበታል፡፡
በተለይ ባለፈው ዓመት የክልሉ ወጣቶች ከዞን ዞን በመዘዋወር ጭምር በተደራጀ አግባብ ያከናወኑት ዘርፈ ብዙ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ስራዎች የበርካታ አቅመ ደካማ ወገኖቻችንን የኑሮ ጫና ያቃለለና የደገፈ፤ ወጣቱ የሰላምና የልማት ሃይል መሆኑን በተግባር ያረጋገጠ መሆኑንም አስታውሰዋል፡፡
የወጣቱ የክረምት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት የማህበረሰባችንን ነባር የመተሳሰብና የመረዳዳት እሴት የሚያጎለብት ብቻ ሳይሆን፤ የህዝብ ለህዝብ ትስስርንና አብሮነትን የሚያጠናክር፤ የህዝቦች አንድነትን የሚያፀና፤ የልማት ትብብር የሚያሳድግ እና ለዘላቂ ሰላምና ልማት ሚናው የጎላ መሆኑንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል፡፡
ከፍተኛ የህዝብና የመንግስት ሀብት በማዳን ላይ በሚገኘው በመርሃ ግብሩ፤ ዘንድሮም ወጣቱ በሀገር ግንባታ ያለዉን ሚና ይበልጥ በሚያጎለብቱና ክልሉን የሰላም፣ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ እየተሰሩ ያሉ ስራዎችን በማጠናከር አቅም መፍጠር በሚችሉ ዘርፈ ብዙ ተግባራት በማሳተፍ ውጤታማ ስራ ይሰራልም ብለዋል፡፡
ለዚህም መላው የክልሉ ወጣቶች ዘንድሮም በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች አስተባባሪነት በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች በሚከናወኑ የክረምት ወራት የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ተግባራት ተሳትፎአችሁን በማጠናከር ክረምቱን ለማህበረሰብ አወንታዊ ለውጥ በመትጋት በበጎ ተግባራት እንዲታሳልፉ ሲሉ ከአደራ ጭምር ጥሪ አቅርበዋል፡፡
የክልሉ መገለጫ የሆነው የሰላም ተምሳሌትነት ያለ ወጣቱ የሰላም አርበኝነት የማይታሰብ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ወጣቱ እንደተለመደው ሰላምን እንዲያፀና በማሳሰብ የክልሉ መንግስት የወጣቱን ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ተሳትፎና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በቁርጠኝነት የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡