የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲው የተረጋጋና ቀጣይነት ያለዉ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የፈጠራቸው ዕድሎችን ተጠቅሞ የ10 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ ይሰራል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሕዝብ ምክር ቤትና የብሔረሰቦች ምክር ቤት 2ኛ ዓመት የስራ ዘመን የጋራ መክፈቻ ሥነ-ሥርዓት ላይ ተገኝተው የመክፈቻ ንግግር አድርገዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በመክፈቻ ንግግራቸው የክልሉን መንግስት የ2018 ዋና ዋና የልማት ዕቅድና የትኩረት አቅጣጫዎች የዳሰሱ ሲሆን፤ በንግግራቸው ትኩረት ካደረጉባቸው ነጥቦች የኢኮኖሚ የዕድገት ዘርፎች ይጠቀሳሉ፡፡

መንግስት ባለፉት የለውጥ አመታት በሁሉም ዘርፍ ዘላቂነት ያለው ዕድገት ለማረጋገጥ የተለያዩ ተግባራትን አከናውኗል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይም የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ አሳታፊና አካታች የኢኮኖሚ ግንባታ እውን በማድረግ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትን ማስመዝገብ ማስቻሉን ገልጸዋል፡፡

የክልሉ ኢኮኖሚ በ2017 የ9 በመቶ ዕድገት ያስመዘገበ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በ2018 የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ፖሊሲው የተረጋጋና ቀጣይነት ያለዉ የኢኮኖሚ ዕድገት ለማስመዝገብ የፈጠራቸው ዕድሎችን ተጠቅሞ የ10 በመቶ ዕድገት ለማስመዝገብ የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አያይዘው ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ካለው እምቅ አቅም አንጻር የክልሉ መንግስት ባለፉት ዓመታት የቱሪዝም ዘርፉን ለማሳደግ በትኩረት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡

በ2018 በዘርፉ የተጀመሩ ስራዎችን በማጠናከር ክልሉ በቱሪዝም ዘርፍ ያለውን እምቅ አቅም አሟጦ በመጠቀም ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልጸዋል፡፡

ቱሪዝምን ዋነኛ የዕድገት አንቀሳቃሽ ሞተር ማድረግ ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለዚህ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት አሰጣጥ ክፍተቶችን በመሙላት አዳዲስ የቱሪዝም መዳረሻ ስፍራዎችን የማስፋት፣ ነባሮቹን ደግሞ ለጎብኚዎች ምቹ የማድረግና የማስተዋወቅ ስራ እንደሚሰራ አስታውቀዋል፡፡

ከማዕድን ሀብት ልማት አንጻር የክልሉን አቅም በስፋት በማጥናት የመግለጥ፤ ጥናታቸው የተጠናቀቀን ወደምርት የማስገባት እንዲሁም በምርት ላይ የሚገኙትን የማምረት አቅም የማሳደግ እና በዘርፉ የምርት ተጠቃሚነትን የማሳደግ ተግባራት ትኩረት የሚሰጠው መሆኑን ገልጸዋል፡፡

አክለው በዘርፉ አግልግሎት አሰጣጥ ስርዓቱን በማዘመንና ፈጣን በማድረግ አላስፈላጊ ችግሮችን ለመፍታትና ሀብቱን በስፋት ጥቅም ላይ ለማዋል በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል።

ከአምራች ኢንዱስትሪ ልማት ጋር በተያያዘም በዘርፉ በኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የተፈጠረን ምቹ ሁኔታ ተጠቅሞ ፈጣንና ጥራት ያለው የኢንዱስትሪ ልማት ማረጋገጥ የትኩረት አቅጣጫ መሆኑን ጠቅሰው፤ በ2018 ለዘርፉ ዕድገት ይሰራል ብለዋል፡፡ 

በተለይ ዘርፉ ለዜጎቸ የስራ እድል እንዲፈጥርና ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ አምራች ኢንዱስትሪዎች ምርታቸውን ለሀገር ዉስጥና ለውጭ ገበያ በማቅረብ ለክልሉም ሆነ ለሀገሪቱ ኢኮኖሚ የሚያበረክተውን አስትዋጽኦ ለማሳደግ ድጋፍ የሚደረግ መሆኑን ገልጸዋል።

ክልሉ ከፍተኛ የሆነ የኢንቨስትመንት አቅም ያለው መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉን አማራጭ የኢንቨስትመንት ዕድሎችና ምቹ ሁኔታዎች በማስተዋወቅ በዘርፉ የተገኙ ውጤቶችን ለማላቅ የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በዚህ ረገድ አልምተው የሀገሪቱንና የክልሉን የኢኮኖሚ ዕድገት በማፋጠን የህብረተሰቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰሩ አልሚ ባለሀብቶችን በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎት፤ በማዕድን ልማትና በሌሎች የኢንቨስትመንት አማራጮች እንዲሰማሩ የሚደረግ መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

በ2018 ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ የስራ አጥነት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት በልዩ ትኩረት በመስራት የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ጥረት የሚደረግ መሆኑንም ገልጸዋል፡፡

ለዚህ ክልሉ በቱሪዝምና በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች ያሉትን ፀጋዎች ተጠቅሞ የስራ ዕድሎችን የመፍጠር እና በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የስራ ዕድሎችን የማስፋት ተግባራት ትኩረት ይደረግባቸዋል ብለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው የብድር፥ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን በብዛትና በጥራት በማዘጋጀት እንዲሁም ብቁ የክህሎትና የአመለካከት ቀረፃ ስልጠናዎችን በመስጠት ወጣቱን ወደ ስራ በማስገባት ከፍተኛ ውጤት ለማስመዝገብ ርብርብ የሚደረግ መሆኑንም አሳውቀዋል።

መሠረታዊ የፍጆታ ዕቃዎችን ጨምሮ የነዳጅ ምርት አቅርቦትና ስርጭት ላይ ክትትልና ቁጥጥር በማጠናከር ለተጠቃሚው እንዲቀርብ እና በስርጭት ሂደት ለሚቀርቡ ቅሬታዎችና አቤቱታዎች የማስተካከያ እርምጃ በመውሰድ ገበያ የማረጋጋት ስራ የሚሰራ መሆኑን ጠቁመዋል፡፡

Leave a Reply