የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት የክልሉን መንግስት የ2019 በጀት 85.8 ቢሊየን ብር በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ምክር ቤት እያካሄደ ባለው 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የቀረበን የክልሉን መንግስት የ2019 ረቂቅ በጀት እና የተጨማሪ በጀት አዋጅ አስመልክቶ በጥልቀት ተወያይቷል፡፡

ምክር ቤቱ የቀረበውን የክልሉን መንግስት የ2019 ረቂቅ በጀት ሀገራዊና ክልላዊ የዘላቂ ሰላምና የሁለንተናዊ ብልፅግና ግቦችን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች በማጠናከር የክልሉን ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ አንጻር በመመርመር:-

85 ቢሊየን 774 ሚሊዮን 12 ሺህ 25 ብር እንዲሁም የተጨማሪ በጀት አዋጅ 2  ቢሊየን አምስት  መቶ ዘጠኝ ሚሊየን 724 ሺህ  383 ብር  በሙሉ ድምፅ አጽድቋል፡፡

ረቂቅ በጀቱን ለምክር ቤቱ ያቀረቡት የክልሉ ምክር ቤት የፕላን፣ በጀትና የመሠረተ-ልማት ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ሰብሳቢ አቶ ዕንቁ ዮሐንስ፤ በጀቱ ከክልሉ የውስጥ ገቢና ከፌዴራል መንግስት ድጎማ የሚሰበሰብ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ረቂቅ በጀቱ አስፈላጊው ዝግጅትና በቂ ምክክር በየደረጃዉ ከሚገኙ የባለድርሻ አካላት ጋር ተደርጎበት እንዲሁም የተቀመጠዉን የዞኖች የድጎማ ቀመር ታሳቢ ባደረገ መልኩ መዘጋጀቱንም አቶ ዕንቁ አብራርተዋል።

በጉባኤው በም/ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፤ የረቂቅ በጀቱን ዝርዝር ለምክር ቤቱ አቅርበዋል።

የበጀቱን ከግማሽ በመቶ በላይ በዉስጥ ገቢ የሚሰበሰብ መሆኑን የጠቀሱት አቶ ተፈሪ፤ ገቢን አሟጦ በመሰብሰብ መጠቀም እና ዉስን የሆነውን ሀብት በአግባቡ ማስተዳደር እንደሚገባም ገልፀው በጀትን በዲጂታል መንገድ በማስተዳደር የተመደበው በጀት ለታለመው አላማ እንዲውልና ጤናማ የሆነ የፋይናንስ ስረዓት እንዲኖር እንዲሚሰራ ተናግረዋል።

ከበጀቱ 20 በመቶ ለክልል ማዕከላት እንዲሁም 80 በመቶው ለዞን አስተዳደር እርከኖች የሚዉል መሆኑ እንዲሁም ተጨማሪ የታወጀው 2.9 ቢሊዮን በጀት አዋጅ ከዚህ ቀደም ለመንግስት ሰራተኞች እና ለፍትህ አካላት የተከፈለ የደምወዝ ጭማሪ መሆኑ ተገልጿል።

ለሁለት ተከታታይ ቀናት የተካሄደው የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ፡-

በክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የቀረበውን የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም፤ የ2019 ጠቋሚ እቅድ፤ በክልሉ መስተዳድር ምክር ቤት የቀረበን የክልሉን መንግስት የ2019 ረቂቅ በጀት እንዲሁም ክልላዊ ተቋማዊ አቅምን በማጠናከር የክልሉን ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት በሚያረጋግጥ አግባብ የተዘጋጁ ረቂቅ አዋጆች መርምሮ በማፅደቅን ጉባኤውን በስኬት አጠናቋል።

በጉባኤው ማጠቃለያ የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት አባላት ባለፉት አምስት ዓመታት ለክልሉ ሕዝቦች በጋራ የመልማት ትልም ስኬት እና ለሕዝቦች ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከፍተኛ ፋይዳ ያላቸውን ውሳኔዎች በማሳለፈ በህዝብ እንደራሴነት የሚጠበቅባቸውን ኃላፊነት በአግባቡ በመመወጣቸው ዕውቅና ተሰጥቷቸዋል።

Leave a Reply