ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለታሪካዊው የመጋቢት 24 ሰባተኛ ዓመት ሀገራዊ ለውጥ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለታሪካዊው የመጋቢት 24 ሰባተኛ ዓመት ሀገራዊ ለውጥ የእንኳን አደረሳችሁ መልዕክት አስተላልፈዋል።


የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

ወረሃ መጋቢት የለዉጥ ችቦ የተለኮሰበት፣ ፍሬያማ የሰባት ዓመት ጉዞ የተጀመረበት፣ በርካታ የዉስጥ እና የዉጪ ፈተናዎችን ለጥንካሬያችን ግብዓት ያደረግንበት፣ መጋቢታዊያንን በመዘከር ከትናንት በመማር ለነገ በተሻለ ለመዘጋጀት፤ ራዕያችንን ለማሳካትና የመንሰራራት ጉዞአችን የበለጠ ለማፍጠን የምንዘክርበት ዕለት እንኳን አደረሳችሁ! አደረሰን!


መጋቢት ሀገራችን ከተጋረጠባት የመበታተን አደጋ የታደገ፤ የዘመናት የመገፋፋትና የመጠፋፋት የፖለቲካ ባህላችንን ቀይሮ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ እና የበለፀገችና የተከበረች ኢትዮጵያን ለትውልድ የማሻገር ህልም የሰነቀ በታላላቅ ስኬቶች የታጀበ ሀገራዊ የለውጥ ጉዞ ዕውን የሆነበት ታሪካዊ ወር ነው፡፡


የህዝብ ግፊት የወለደው ህጋዊና ህገመንግስታዊ የሆነዉ ሀገራዊ ለውጡ፤ ባለፉት ሰባት ዓመታት በመደመር እሳቤ እየተመራ ሰላም፤ ይቅርታና ፍቅርን አስቀድሞ ፈተናን ወደ ዕድል፤ ዕዳን ወደ ምንዳ እየቀየረ ኢትዮጵያን ለማሻገር መሠረት የጣሉ በርካታ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች ማስመዝገብ ችሏል፡፡


በፖለቲካው ረገድ በጠላትነት ፍረጃ የተሸበበውን ነባሩን የፖለቲካ ባህል ሺሮ፤ በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ባህል በመገንባት በጋራ ሀገራዊ የሰላምና የልማት ጉዳዮች ዙሪያ ከፖለቲካ ልዩነቶች ባሻገር አብሮ የመስራት የትብብር ባህል ማሳደግ ችሏል፡፡


ለዲሞክራሲ ባህል ግንባታ መጎልበት ቁልፍ ለሆነው የተቋም ግንባታ ትኩረት በመስጠትም፤ ከፖለቲካ ተጽእኖ የፀዱ ጠንካራ ተቋማትን በመገንባት ሀገር የሚያሻግር ስራ ሰርቷል፡፡ የሀገራዊ ለውጡ ፍሬ የሆነው ክልላችን በህዝቦች ነፃ ፍላጎትና ይሁንታ፤ ፍፁም ሰላማዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ፤ በሕገ-መንግስታዊ ማዕቀፍ የተመሰረተ የለውጡ እዉነተኛ የዴሞክራሲ ፍሬ ነው።


ለውጡ ልዩነቶችን በኃይልና በነፍጥ የመፍታት የፖለቲካ ስብራት ታሪካችንን በመቀልበስ ለብሔራዊ መግባባትና ለጠንካራ ሀገረ-መንግስት ግንባታ መሠረት የጣለ፤ ሁሉን አሸናፊ ወደ ሚያደርግ ሀገራዊ የምክክር ሂደት ሀገራችንን በማስገባት አዲስ ምዕራፍ መከፍት ችሏል፡፡
በኢኮኖሚው ረገድ ሀገራዊ አቅሞችን መጠቀም ያስቻሉ የኢኮኖሚ ማሻሻያዎችንና በርካታ የልማት ኢኒሼቲቮችን በመተግበር የማይቻል በሚመስሉ መስኮች ጭምር ምርታማነትን በማሳደግ የታሪክ እጥፋት ማስመዝገብ አስችሏል፡፡


በሀገራችን ታሪክ የመጋቢት ፍሬዎቻችችን ስናወሳ የመላ ኢትዮጵያዊያንን ህብረትና አንድነት ይበልጥ ያስተሳሰረና የይቻላል መንፈስን ዳግም ያጎናፀፈን የዳግማዊ አድዋ ብሔራዊ የድል ዓርማችን የሆነው ታላቁ የሕዳሴ ግድባችን በጉልህ ይጠቀሳል፡፡


የለውጡ መንግስት ባለፉት የለውጥ ዓመታት በርካታ ቀጠናዊና ዓለምአቀፋዊ ጫናዎችን ተቋቁሞ ሀገር አሻጋሪና ትውልድ ተሻጋሪ ቋሚ የወል ሀውልታችን የሆነው የሕዳሴ ግድባችንን በግንባታ ሂደት ከገጠመው ችግር በማውጣት፤ በመላ ኢትዮጵያዊያን ርብርብር ከዳር በማድረስ ሀገራችንን ወደ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ለማሸጋገር ከጫፍ ደርሷል፡፡


በቀጣይም ኅብረ ብሔራዊ አንድነትን በማፅናትና ትብብርን በማጎልበት የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ ክልላዊና ሀገራዊ የሰላም፤ የልማትና የብልፅግና ህልሞችን ከዳር በማድረስ የህዝባችንን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በጋራ መስራት ይገባናል።


ፈጣሪ ሀገራችንን እና ህዝቦቿን ይባርክ

Leave a Reply