
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ የወላይታ ብሔረሰብ የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዩኔስኮ በዓለም የሰው ልጅ ወካይ የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶነት በመመዝገቡ የተሰማቸውን ልዩ ደስታ በመግለጽ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡



የመልዕክቱ ሙሉ ሃሳብ እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
ሃሹ ሃሹ ሃሹ! እንኳን ደስ አላችሁ!! እንኳን ደስ አለን!!
በክልላችን የታታሪ ህዝቦች መገኛ የሆነው የወላይታ ብሔረሰብ፥ የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በዓለም ቅርስነት በመመዝገቡ የተሰማኝን ጥልቅ ደስታ ለመግለፅ እወዳለሁ።
በሕንድ፣ ኒው ዴልሂ እየተካሄደ በሚገኘው 20ኛው የተባበሩት መንግሥታት የትምህርት፣ የሳይንስና የባሕል ድርጅት (ዩኔስኮ)፥ የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ጥበቃ ኮሚቴ ጉባኤ ላይ ኢትዮጵያ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ያቀረበችው የወላይታ የዘመን መለወጫ በዓል “ጊፋታ” በሰው ልጅ የማይዳሰሱ የባሕል ቅርሶች ዝርዝር ስር ተመዝግቧል።
ጊፋታ በአለም የማይዳሰሱ የባህል ቅርሶች ውስጥ መመዝገቡ የክልሉ መንግስት በክልላችን የሚገኙ ቱባ የባህል ሀብቶች በመጠበቅ፥ በማልማት እና በማስተዋወቅ ማህበራዊ እና ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ በማድረግ ላይ ያለው ጥርት ፍሬ በማፍራት ላይ መሆኑን የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ የክልላችንን ቱሪዝም የሚያሳድግ እና ክልላችን ለሰው ልጆች ሰላም፥ አብሮነትና አንድነት የጎላ ፋይዳ ያላቸው የበርካታ ቱባ ባህሎች መገኛ መሆኑን አመላካች ነው።
በዚህ አጋጣሚ ቅርሶቻችን በዩኔስኮ እንዲመዘገብ ተግታችሁ ለምትሰሩ የኢትዮጵያ ቱሪዝም ሚኒስቴር ፣ ለኢትዮጵያ ለቅርሶች ጥበቃ ባለስልጣን አመራሮችና ባለሙያዎች እንዲሁም ጊፋታ በዓለም ቅርስነት እንዲመዘገብ ከፍተኛ አስትዋፅኦ ላበረከታችሁ ለወላይታ ዞን አስተዳደርና ለክልላችን አመራሮችና ባለሙያዎች፥ በየደረጃው ለሚትገኙ ባለድርሻ አካላት፣ ይህን ፀጋ ጠብቀው ላቆዩ አባቶች፥ በአጠቃላይ ለወላይታ እና ለመላው የክልላችን ሕዝቦች በክልሉ መንግሥት ስም ልባዊ ምስጋና ለማቅረብ እወዳለሁ።
የክልሉ መንግስት በቀጣይም የክልላችንን ህዝቦች ቱባ ባህሎች በመጠበቅ፥ በማልማት እና በማስተዋወቅ በቱሪዝም ዘርፍ ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታቸውን ለማሳደግ ብሎም ለህዝቦች አብሮነትና አንድነት ያላቸውን የጎላ ፋይዳ በመጠቀም የህዝቦች አንድነትንና የልማት ትብብር በማጠናከር ለክልላዊ የሰላም፥ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ራዕይ ስኬት መስራቱን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ላረጋግጥ እወዳለሁ።
“ጊፋታ” ከትውልድ ወደ ትውልድ ሲተላለፍ የመጣ በወላይታ ህዝብ ዘንድ ልዩ ስፍራ የሚሰጠው፥ የህዝቡ የማንነት መገለጫ የሆኑ ድንቅ የሰላም፥ የአብሮነት እና የአንድነት እሴቶች ያሉት፥ ወንድማማችነትን የሚያጠናክር፥ ፍቅርን፥ አብሮነትንና አንድነትን በማጉላት የሚከበር ታላቅ የባህል ሀብታችን በመሆኑ ለመላው የክልላችን ህዝቦች በድጋሚ እንኳን ደስ አላችሁ!! እንኳን ደስ አለን!! ለማለት እወዳለሁ።
ሃሹ ሃሹ ሃሹ
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር




