
የክልሉ መንግስት የሦሥትዮሽ ስትራቴጂካዊ የቀጥታ የንግድ ልውውጥ የትብብር ስምምነት ተፈራርሟል
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በስትራቴጂካዊ የሦሥትዮሽ የቀጥታ የንግድ ልውውጥ ትብብር ዙሪያ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ እንዲሁም ከዙዦዎ ከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ካምፓኒ (ZCCD) ጋር በወላይታ ሶዶ ከተማ መክረዋል፡፡


በምክክሩ የክልሉ መንግስት ከዙዦዎ ከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ካምፓኒ (ZCCD) እና ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ጋር የሦሥትዮሽ ስትራቴጂያዊ የቀጥታ የንግድ ልውውጥ ትብብር የጋራ መግባቢያ የስምምነት ሰነድ ተፈርሟል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በምክክሩ የክልሉ መግስት የኢትዮጵያ እና የቻይናን ከግማሽ ምዕት አመት በላይ የዘለቀ ጠንካራ ወዳጅነትና ትስስር በሚያጠናክር አግባብ፤ ከኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ጋር በልማት ትብብሮች ዙሪያ ውጤታማ ስራዎችን በቅርበት በመስራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው ከወዳጅነት ትብብር ኮሚቴው ጋር በኢንቨስትመንት፤ በገበያ ትስስር፤ በገጠር አማራጭ ታዳሽ ሃይል እንዲሁም በኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች ዙሪያ ያተኮሩ ተከታታይ ውይይቶችን በማድረግ ውጤታማ የልማት ትብብሮችን መፍጠር መቻሉንም ገልጸዋል፡፡


የተደረሱ የጋራ መግባቢያ የትብብር ማዕቀፎችን ተከትሎ ባለፉ ጊዜያት ስኬታማ ስራዎች ተሰርተዋል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ የክልሉን የቡና ምርት በቻይና ገበያዎች በማስተዋወቅ የገበያ ትስስር ለመፍጠር በተደረጉ ጥረቶች የተገኘው አመርቂ ውጤት ተጠቃሽ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ትብበሩን ከገበያ ትስስር በላይ በማድረግም የክልሉን የቡና ምርት በቀጥታ በቻይና ገበያዎች ከማቅረብ ባለፈ፤ የቡና ምርታማነት ለማሳደግ እና ቡና አምራች አርሶ አደሮችን ይበልጥ ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችሉ ስራዎች መጀመራቸውን በመጥቀስ ለኮሚቴው አድናቆታቸውን ገልጸዋል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ከሀገራዊው የአረንጓዴ ልማት ፖሊሲ ጋር አብሮ በሚሄድ መልኩ፤ ከኮሚቴው ጋር የገጠር መንደሮችን በአማራጭ የታዳሽ ኃይል (በሶላር ፓነል) ተጠቃሚ ማድረግ የሚያስችል ትብብር በመፍጠርም የተጀመረው ስራ የገጠር ሽግግርን ለማረጋገጥ ቁልፍ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ክልሉ በርካታ ፀጋዎች፤ እምቅ የኢንቨስትመንት አቅሞች እንዲሁም በከተማም በገጠርም ከፍተኛ የመልማት አቅም ያለው መሆኑን ያስረዱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከኮሚቴው ጋር ያሉ የትብብር ማዕቀፎችን በማስፋት የቻይናን ባለሀብቶችና ካምፓኒዎች በተለያዩ የንግድና የልማት ዘርፎች የማሳተፍ ስራ በመሰራት ላይ ስለመሆኑ ገልጸዋል፡፡


የዛሬው ምክክርም የዚሁ ጥረት አካል መሆኑን ጠቅሰው፤ ምክክሩ ከዙዦዎ ከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ካምፓኒ (ZCCD) እንዲሁም ከወዳጅነት ትብብር ኮሚቴው ጋር ስትራቴጂያዊ የቀጥታ የንግድ ልውውጥ ትብብር መፍጠር የሚያስችል ስምምነት ላይ በመድረስ፤ ትብብሩን ወደ ቀጣይ ምዕራፍ የሚያሻግር መሆኑን ተናግረዋል፡፡


ስምምነቱ የክልሉ መንግስት በክልሉ የሚገኙ ፀጋዎችን ተጠቅሞ የክልሉን ዕድገትና ልማት በማፋጠን የክልሉን ህዝብ ተጠቃሚነት ለማሳደግ በማድረግ ላይ ያለው ጥረትን በእጅጉ የሚያግዝ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡
ኮሚቴው በቀጣይም ትብብሩን አጠናክሮ የቻይና ባለሀብቶች እና ካምፓኒዎች በተለያዩ የኢንቨስትመንት፤ የቱሪዝም የኢንዱስትሪ ልማት እና በሌሎችም ዘርፎች እንዲሳተፉ እንዲሰራ የጠየቁ ሲሆን፤ የክልሉ መንግስት በዚህ ረገድ አስፈላጊውን ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ከክልሉ መንግስት ጋር በቅርበት በመስራት የክልሉን ዕድገት በማገዝ ላይ መሆኑን በመግለጽ፤ ልባዊ ምስጋና አቅርበዋል፡፡

የኢትዮ-ቻይና የወዳጅነት ትብብር ኮሚቴ ሊቀ-መንበር ቤቲ ሱ በበኩላቸው፤ የወዳጅነት ኮሚቴው ከክልሉ መንግስት ጋር ላለው ትብብር ልዩ ስፍራ የሚሰጠው መሆኑን ተናግረው፤ ግባቸው በትብብሩ ተጨባጭ ውጤት በማምጣት የክልሉን ሁለንተናዊ ልማት መደገፍ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
ሊቀ-መንበሯ ኮሚቴው ከክልሉ መንግስት ጋር ላለው ውጤታማ ትብብር የክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የቅርብ ክትትልና ድጋፍ አስትዋጽኦው ከፍተኛ መሆኑን በመጥቀስም ልባዊ ምስጋና ያቀረቡ ሲሆን፤ በትብብሩ ውጤታማ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አክለው በተሰሩ ስራዎች የክልሉን የቡና ምርቶች በቻይና ገበያ በማስተዋወቅ ባጭር ጊዜ ውስጥ ተቀባይነታቸውን ከማሳደግ ባሻገር ጠንካራ የገበያ ትስስር በመፍጠር የቡና ንግዱ ልውውጡን ማሳደግ መቻሉን አብራርተዋል፡፡
ከዙዦዎ ከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ካምፓኒ (ZCCD) ጋር የተደረሰው የቀጥታ የንግድ ልውውጥ ትብብርም ስትራቴጂካዊ አጋርነትን በማጠናከር፤ ለክልሉ የግብርና ምርቶችና ለኢንዱስትሪ ግብዓት የሚሆኑ ጥሬ ዕቃዎች የገበያ ትስስርና ምቹ የንግድ ልውውጥ በማመቻቸት ለክልሉ ኢኮኖሚያዊ ዕድገት ፋይዳው ከፍተኛ መሆኑን አስረድተዋል፡፡


የተደረሰው ስምምነት በቻይና የጎለበተ የኢንዲስትሪ መሠረት ያለው የዙዦዎ ከተማ አስተዳደር ባሳየው ሙሉ ድጋፍ ሊሳካ መቻሉንም በመግለጽ፤ ስምምነቱ በተጨማሪም በክልሉ በከተሞችና በኢንዱስትሪ ልማት ዘርፍ አቅም የሚፈጥር መሆኑን ተናግረዋል፡፡
በቀጣይም የትብብር ማዕቀፉን በማሳደግ ከተጀመሩ ትብብሮች በተጨማሪ በሌሎች የተለያዩ የልማት አውታሮች፤ በኢንቨስትመንት እንዲሁም በቴክኖሎጂ ሽግግር ዙሪያ ትብብሮችን በማስፋት የሚሰሩ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
በምክክሩ ከኮሚቴው አባላት በተጨማሪ የዙዦዎ ከተማ ኮንስትራክሽንና ልማት ካምፓኒ (ZCCD) ተወካዮች እና ሌሎች በንግዱ ዘርፍ የተሰማሩ የቻይና ካምፓኒዎች ተወካዮችም ተሳትፈዋል፡፡




