
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ለከተራ እና ለጥምቀት በዓል የእንኳን አደረሳችሁ የመልካም ምኞት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመልዕክታቸው የጥምቀተ በዓል ፀብና ጥላቻን በሰላምና በፍቅር የምንተካበት፣ ልዩነቶችንና አለመግባባቶችን በአንድነትና በፍቅር የምንፈታበትና የሚናሸገርበት፣ ትህትናን ተላብሰን ወንድማማችነትንና እህትማማችነንት የሚናፀናበት ደማቅ በዓል ነው ብለዋል።
የክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል፡-
እንኳን ለከተራ እና ለጥምቀት በዓል በሰላም አደረሳችሁ! አደረሰን!
የጥምቀት በዓል ጌታችን መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ በዮርዳኖስ ወንዝ በዮሐንስ እጅ ተጠምቆ ትህትናን ለዓለም ያስተማረበት ታላቅ ሃይማኖታዊ በዓል ነው፡፡
ኃይማኖታዊ እሴቱንና ትውፊቱን ጠብቆ የሚከበረው ጥምቀተ በዓል ፀብና ጥላቻን በሰላምና በፍቅር የምንተካበት፣ ልዩነቶቻችንና አለመግባባቶችን በአንድነትና በፍቅር የምንፈታበት፣ ወንድማማችነትና እህትማማችነት የሚፀናበት ደማቅ በዓል ነው።
በዓሉን ስናከብር የክርስቶስን የፍቅርና የአንድነት ተምሳሌትነት በመከተል፤ መተሳሰብንና በጎነትን ይበልጥ በማጎልበት፤ የተቸገሩትን በመርዳት እንዲሁም በአንድነት ለሁለንተናዊ ዕድገት የድርሻችንን ለመወጣት ቃል በመግባት ማክበር ይገባናል፡፡
ጥምቀት ከኃይማኖታዊ ሥርዓት በተጨማሪ በዓለም የሰው ልጅ የማይዳሰስ ቅርስነት የተመዘገበ የጋራ ሀብታችን በመሆኑ፤ በዓሉ ኃይማኖታዊና ባህላዊ እሴቱን በጠበቀ መልኩ በሁሉም አከባቢ እንዲከበር ሁላችንም የድርሻችንን ማበርከት ይገባናል፡፡
በዓሉ የሰላም፣ የፍቅር፣ የአብሮነት እና የመተሳሰብ እንዲሆን መልካም ምኞቴን እገልጻለሁ።
መልካም በዓል!
ፈጣሪ ሀገራችንና ሕዝቦቿን ይባርክ!
ጥላሁን ከበደ
ርዕሰ መስተዳድር



