“ጌዴኦ የሚታወቅበትን የይርጋጨፌ ቡና ለዓለም በማስተዋወቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በልዩ ትኩረት እንሰራለን” ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)

በጌዴኦ ዞን ይፋዊ የስራ ቆይታ በማድረግ ላይ የሚገኙት ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ ከዞኑና ከዲላ ከተማ አስተዳደር ከተውጣጡ የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎች ተወካዮች እና አመራሮች ጋር በሰላም፣ በመልካም አስተዳደርና በልማት ጉዳዮች ዙሪያ በዲላ ከተማ ተወያይተዋል።

ክቡር ርዕሰ መስተዳድር በውይይቱ መክፈቻ ዲላ ከተማ ሲደርሱ በህብረተሰቡ ለተደረገላቸው እጅግ ደማቅ አቀባበል ልባዊ ምስጋናቸው አቅርበዋል።

በክልሉ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ላይ እንገኛለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በመደመር መንግስት መሪነት፤ በአዲስ የስራ ባህል፤ የአመራር ስርዓትና በአዲስ ጉልበት የክልሉን ህዝብ አንድነት እና የልማት ትብብር በማጠናከር፤ የበለፀገች ደቡብ ኢትዮጵያን ዕውን ለማድረግ በሙሉ አቅም ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡

በውይይቱ ከህብረተሰቡ የተነሱ የመልካም አስተዳደር፤ የልማት፤ የሰላም እንዲሁም የህዝቦች አንድነትንና የርስ በዕርስ ትስስርን ከማጠናከር ጋር በተያያዘ የተነሱ ጥያቄዎችን በተገቢው መንገድ ለመመለስ የሚሰራ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ከተነሱ ጥያቄዎች በአጭር ጊዜ ምላሽ የሚያሻቸውንና የቅድሚያ ቅድሚያ ልሰጣቸው የሚገቡ አጣዳፊ ጥያቄዎችን በመለየት፤ በተያዘው የመቶ ቀን ዕቅድ አካል ከዳር ለማድረስ የሚሰራ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፣ ቀሪ ጥያቄዎችን በመካከለኛ እንዲሁም በረዥም ጊዜ ዕቅድ ለመመለስ ታቅዶ የሚሰራ መሆኑን አስረድተዋል።

በክልሉ የ100 ቀን እቅድ ውስጥ በጌዴኦ ዞን በግብርና ዙሪያ በተለየ ሁኔታ ለመስራት መታቀዱን ጠቅሰው፤ ግብርና የምግብ ሉዓላዊነትን ከማረጋገጥ ባለፈ ለስራ ዕድል ፈጣራ እና ለኢኮኖሚ መዋቅራዊ ሽግግር ወሳኝ በመሆኑ ልዩ ትኩረት የተሰጠው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

አክለው በተለይ ጌዴኦ የሚታወቅበትን የይርጋጨፌ ቡና ምርታማነት በማላቅ የአርሶ አደሩን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንዲሁም ለሀገር ኢኮኖሚ የጎላ አስተዋፅኦ ማበርከት እንዲችል አቅደን እንሰራለን ሲሉ ተናግረዋል።

ከሌማት ቱሩፋት አኳያ እንደየ አካባቢው ስነ-ምህዳራዊና ከባባዊ ምቹነት የንብ ማነብ፣ የዶሮ ዕርባታና እንቁላል፣ የወተት ልማት እንዲሁም በስጋ ምርት የድለባ ስራን በማስፋት በቤተሰብ ደረጃ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን አስታውቀዋል።

ከማህበራዊ ልማት አኳያ ለጤናና ለትምህርት ዘርፍ ስራዎች ትኩረት የሚሰጥ መሆኑንም ጠቅሰው፤ በተለይ ለቅድመ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ስራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት በህብረተሰቡ ተሳትፎ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡

ለማንኛውም ኢንቨስትመንት መነሻው ቁጠባ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ቁጠባ ላይ በልዩ ትኩረት መስራት እንዲሁም ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የውስጥ አቅምን ማጎልበት ትኩረት የሚያሻው መሆኑን ገልፀዋል፡፡  

ርዕሰ መስተዳድሩ የጌዴኦን ማህበረሰብ የሰላም እሴቶች በመጠቀም አስተማማኝ እና አውንታዊ የሰላም ባህል መገንባት ለዘላቂ ልማት መሠረታዊ በመሆኑ ለዚሁ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡  

የጌዴኦን ዞንና የዲላ ከተማ አስተዳደር የቱሪዝም ማዕከል የማድረግ፣ የዲላ ከተማን የኮሪደር ልማት በማጠናከር ውብና ፅድ ማድረግ እንዲሁም ኢንዱስትሪን ማስፋት ላይ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባም ገልፀዋል፡፡

ለስራዎች ውጤታማነት በተለየ ሁኔታ በማቀድ በመደመር መንግስት የመፍጠን፤ የመፍጠር እና የመዝለል መርሆች መተግበር እንደሚገባ አስምረዋል።

አዲሱ የመደመር መንግስት ስራዎችን ከወትሮ በተለየ መንገድ እየሰራ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከዚህ በኋላ  እያንዳንዱ ስራ በጥናትና ምርምር በማስደገፍ የሚሰራ በመሆኑ የዲላ ዩንቨርሲቲን ጨምሮ በክልሉ የሚገኙ ከፍተኛ  የትምህርት ተቋማት የሰው ህይወት ለመቀየር የበኩላቸውን ድርሻ እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።  

መንግስት እና ህዝብ እጅና ጓንት ሆነው በጋር ሲሰሩ ልማት ይሰምራል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የዞኑና የከተማ አስተዳደሩ ህዝብ ጠያቂ ብቻ ሳይሆን የልማቱ ባለቤት በመሆን በሁሉም ዘርፍ የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ በሚደረገው ጥረት የልማት ተሳትፎውን በማሳደግ አሻራውን ማኖር እንደሚገባው አስገንዝበዋል፡፡ 

ከሰላም አኳያ የክልሉ መንግስት ጥቂት የግል ፍላጎታቸውን ለማሳካት ሲሉ የህዝቦች አንድነትን ለመከፋፈል እና ወንድማማችነትን በመሸርሸር ሰላማችንን ለማደፍረስ የሚሰሩ አካላትን እንደማይታገስ ገልፀው፤ ለዚህ የአመራሩ ቁርጠኝነት፣ እንዲሁም የህብረተሰቡ ተሳትፎ እና እገዛ ቁልፍ መሆኑን አጽንኦት ሰጥተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሙስና እና ብልሹ አሰራር ቀይ መስመር መሆኑን ገልፀው፤ የክልሉ መንግስት ህዝብን በአግባቡ ለማገለግል እና የህዝብ ሀብት ለህዝብ ጥቅም እንዲሁም የመንግስት ስልጣን ለህዝብ አገልግሎት እንዲውል በትኩረት እንደሚሰራ አረጋግጠዋል።

ከዚህ ጋር በተያያዘ የሀይማኖት ተቋማትን ጨምሮ ያሉ ድንቅ ሀገር በቀል እሴቶችን በመጠቀም በትውልዱ ስርቆትን እና ሌብነትን የሚፀየፍ ስብዕና ለመገንባት መስራት እንደሚገባ ተናግረው፤ አባቶች፤ የሀገር ሽማግሌዎችና ምሁራን ይህን ታሪካዊ ኃላፊነት እንዲወጡ ጥሪ አቅርበዋል።   

መዳረሻችን ሁለንተናዊ ብልጽግና፤ ተደማሪ አቅማችን ትልቅ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የክልሉ መንግስት በክልሉ ያሉ ፀጋዎችንና እምቅ የመልማት አቅሞች ወደ ተጨባጭ ዕድገት በመቀየር የክልሉን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ለዘላቂ ሰላም፤ ልማትና ብልጽግና መረጋገጥ አበክሮ የሚሰራ መሆኑን አስምረዋል፡፡

የክልሉ የብልፅግና ፓርቲ ቅርንፍ ጽ/ቤት ኃላፊ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር)፤ በበኩላቸው፤ በክልሉ አመራሩ የሚለካው በፈታው ችግር ልክ መሆኑን ጠቅሰው፤ ለዚህም ከአመራሩ ጋር መግባባት ላይ መደረሱን ተናግረዋል፡፡

የህዝብ ጥያቄዎችን በክልሉ ያሉ ሁሉንም አቅሞች በመጠቀም ለመመለስ በልዩ ትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ገልፀዋል።

Leave a Reply