
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫን በማስመልከት የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳ ዞናዊ ማጠቃለያ እና ሕዝባዊ የድጋፍ ሰልፍ በክልሉ በጋሞ ዞን፤ በአርባ ምንጭ ከተማ በታላቅ ህዝባዊ ተሳትፎ በድምቀት ተካሂዷል፡፡


ምርጫ የዴሞክራሲ ባህልን የምንገነባበት እና ሀገራዊ አንድነታችንን የምናጠናክርበት የዜግነት መብት ብቻ ሳይሆን ከፍ ያለ ሀገራዊ ኃላፊነትም ነው።


በተለይ እንደ ኢትዮጵያ ባሉ ሰፊ ብዝኃነትን ባቀፉ ሀገራት፥ ሀገራዊ ምርጫ ዲሞክራሲያዊ ስርዓትን በማስፋን፤ ውስጣዊ አንድነትን ጠብቆ በዜጎች ተሳትፎ እና በሕዝቦች ትብብር ለጠንካራ ኅብረ-ብሔራዊ ሀገረ-መንግስት ግንባታ ሚናው ከፍተኛ ነው፡፡


ዜጎች የዜግነት መብታቸውን ተጠቅመው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን የመወሰን መብት በተግባር የሚተረጉሙበት ምርጫ፥ የስልጣን ባለቤት ህዝብ መሆኑን ከማረጋገጥ ባለፈ በፀና መሠረት ላይ የተገነባች ሀገር ለትውልድ በማሻገሩ ረገድ ደማቅ አሻራቸውን በድምፃቸው የሚያኖሩበት ሂደት ጭምር ነው፡፡


ግንቦት 24 በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ፤ 50 ሚሊዮን ዜጎች በምርጫው በመሳተፍ፤ በድምፃቸው መፃይ የሀገራቸውን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ከመወሰን ባሻገር በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉዞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ይከፍታሉ ተብሎም ይጠበቃል፡፡



መንግስት ባለፉት የለውጥ አመታት ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በቁርጠኝነት በመስራት በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ባህል የሚያጎለብቱ እና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታን የሚያጠናክሩ ተቋማዊ ሪፎርሞችን በማድረግ ጭምር ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉ ይታወቃል፡፡



7ኛው ሀገራዊ ምርጫም የተጀመሩ ጥረቶችን በማጎልበት እንደ ሀገር ለሰነቅነው ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማበብ አንድምታው ከፍተኛ ነው፡፡



መንግስት ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፤ ፍትሃዊ፤ ነፃና ሁለንተናዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ በሁሉም ረገድ በቂ ዝግጅት ማድረግ መቻሉም ታወቋል፡፡



ከምርጫው አስቀድሞ በምርጫው የምሳተፉ ፓርቲዎች በህግ በተፈቀደው አግባብ ፕሮግራሞቻቸውንና ዕጩ ተወዳዳሪዎቻቸውን ለህዝብ ሲያስተዋውቁ የቆዩ ሲሆን፤ በክልላችን የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳውን በተመሳሳይ በሁሉም የምርጫ ክልሎች በሰፊ ህዝባዊ ተሳትፎ ሲያካህድ ቆይቶ በማጠቃለል ላይ ይገኛል።



በዛሬው ዕለትም ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በተገኙበት በጋሞ ዞን የፓርቲው ዕጩ ተወዳዳሪዎች፤ ደጋፊዎች እና አባላት በተገኙበት፤ ፓርቲው የምረጡኝ የምርጫ ቅስቀሳ ዞናዊ ማጠቃለያውን በአርባ ምንጭ ከተማ በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎና የድጋፍ ሰልፍ በድምቀት አካሂዷል፡፡




