
ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ የክልሉ መንግስት የተቋማት የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች አካል በግንባታ ላይ ያሉ የወላይታ ሶዶ እና የሳውላ ማዕከላት የቢሮ የህንፃ ግንባታ ሂደት በመገምገም ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ ክልሉ በአዲስ መልክ መደራጀቱን ተከትሎ የነበረበትን የቢሮ ችግር ለመቅረፍ እንዲያስችል በስድስቱም የክልሉ ማዕከላት የተቋማት ህንፃ ግንባታዎችን ማስጀመሩ የሚበረታታ ተግባር መሆኑን ተናግረዋል።
በየማዕከላቱ የተጀመሩ የተቋማት የህንፃ ግንባታዎች በላቀ ውጤታማነት የህዝቡን ፍትሀዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለተጀመሩ ስራዎች እና ለጠንካራ ተቋማት ግንባታ ስኬት ሚናቸው የጎላ መሆኑን ጠቅሰው፤ ሆኖም ግንባታው በተቀመጠለት ጊዜ አለመጠናቀቁ ችግሮችን እያስከተለ መሆኑን ገልፀዋል።


በተለይ የተቋማት ህንፃ ግንባታው መዘግየት ክልሉን ለከፍተኛ የቢሮ ኪራይ ወጪ ከመዳረጉም ባሻገር ዞኖች ላይ ጫና እያሳደረ መምጣቱንና ለመንግስት ሰራተኛው ምቹ የስራ ከባቢን ከመፍጠር አኳያ ክፍተት እየፈጠረ መሆኑን እንዲሁም የመልካም አስተዳደር ችግር ምክንያት እየሆነ መምጣቱን በአጽንኦት ተናግረዋል።
ምክንያት ውጤት አይሆንም ያሉት ርዕለ መስተዳድሩ፤ በቀጣይ የተጀመሩ ግንባታዎችን በፍጥነትና በጥራት ገንብቶ ለማጠናቀቅ የነበረውን የስራ ባህል በመቀየር በልዩ ትኩረት በጊዜ የለንም መንፈስ ቀንና ማታ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡


የመደመር መንግስት ፕሮጀክቶችን በፍጥነት እና በጥራት ገንብቶ በአጭር ጊዜ የማጠናቀቅ ባህል ለሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ልምድ ሊሆን እንደሚገባም አስገንዝበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በቀጣይም የሁሉንም ማዕከላት የተቋማት የህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶችን በመገምገም በተያዘላቸው ጊዜ ውስጥ ተጠናቀው አገልግሎት መስጠት እንዲችሉ የክልሉ መንግስት አስፈላጊውን ክትትል እና ድጋፍ ማድረጉን አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም አረጋግጠዋል።




