
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት፤ 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባዔውን በአርባምንጭ ከተማ በማካሄድ ላይ ሲሆን፤ ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ለምክር ቤቱ አባላት አቅርበዋል።



በቀረበው ሪፖርት ዙሪያ በምክር ቤት አባላት ምላሽ እና ማብራሪያ የሚሹ ጉዳዮች ተነስተው በክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ ምላሽ ተሰጥቶባቸዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ባለፉት ሶስት ዓመታት ሁሉንም መዋቅሮች በህግመንግስታዊ ስርዓቱ መሰረት ታዓማኒ፤ አሳታፊና ፍትሃዊ የበጀት ድልድል በማድረግ እና በእኩል የድጋፍና ክትትል ስራዎች በየወቅቱ የሚገጥሙ ማነቆዎችን እየፈታ በመምራት ላይ እንደሚገኝ ገልፀዋል።
ሆኖም በአፈጻጸም ረገድ ያላቸውን ሀብት በአግባቡ በመጠቀም የህብረተሰቡን የልማት ጥያቄ ለመመለስ እና ዞኖቻቸውንና ከተሞቻቸውን ለማሳደግ የሚተጉ መዋቅሮች መኖራቸውን ያህል፤ ሀብት ይዘው ስራ ባለመስራትና ገቢ በአግባቡ ባለመሰብሰብ የልማት ስራዎችን ከመስራት አኳያ ጉድለት የሚስተዋልባቸው መኖራቸውን ተናግረዋል።
ከኑሮ ውድነት ጫና ጋር በተያያዘም ችግሩ የአለም ተለዋዋጭ ነባራዊ ሁኔታ ካመጣቸው ተግዳቶች ጋር የሚያያዝ መሆኑን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የግብርና ምርታማነትን ማሳደግና የግብርና ምርት ወደ ገበያ እንዲወጣ በማድረግ እና ህገወጥ የኮንትሮባንድ ግብይት በመቀነስ ችግሩን ለመቅረፍ ይበልጥ መስራት ይገባል ብለዋል።


ከፕሮጀክቶች መጓተት ጋር በተያያዘ ለተነሱ ጥያቄዎች የኮንትራክተሮች ቃላቸውን ጠብቀው በተቀመጠው ግዜ ያላማጠናቀቅ፣ የመዋቅሮች የሚጠበቅባቸውን በጊዜ አለመፈፀም፣ የአሰሪው ግዴታ አለመወጣት እና ያልተጠበቁ የተፈጥሮ አደጋዎች ፕሮጀክቶች በጊዜ እና በጥራት እንዳይጠናቀቁ ማነቆ መሆናቸውንም ጠቅሰው፤ የክልሉ መንግስት ችግሮችን ደረጃ ደረጃ እየፈታ በመሄድ ላይ መሆኑን አስረድተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በሰጡት ምላሽ ከዳሰሱዋቸው ጉዳዮች አንዱ በወላይታ ዞን በግንባታ ላይ የሚገኘው የሱማሞ አየር ማረፊያ የተመለከተ ሲሆን፤ በምላሻቸው የክልሉ መንግስት ለረዥም ጊዜ ለፕሮጀክቱ መጀመር ማነቆ ሆነው የቆዩ ችግሮችን ከሚመለከታቸው ባላድርሻ አካላት ጋር በመስራት ቀርፎ ወደ ግንባታ ማስገባት መቻሉን ተናግረዋል፡፡
በዚሁ ሂደት የኢትዮጵያ አየር መንገድ ለፕሮጀክቱ አስፈላጊውን በጀት እንዲመድብ በማድረግ ወደ ስራ ማስገባት መቻሉን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ሆኖም ወደ ግንባታ ከተገባ በኋላ የኮንትራክተሩ የአቅም ማነስ ችግር ለፕሮጀክቱ መዘግየት ምክንያት መሆኑን አብራርተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳደሩ በማብራሪያቸው የክልሉ መንግስት ችግሩን ለመቅረፍ ቀጣይነት ያለው ክትትልና ድጋፍ በማድረግ እና ከኢትዮጵያ አየር መንገድ ጋር በቅርበት በመነጋገር አስፈላጊ ማስተካከያዎች እንዲደረጉ ማድረጉንም ገልፀው፤ በተደረገው ማስተካከያ የፕሮጀክቱን ግንባታ በተያዘው የ2019 በጀት ዓመት ለማጠናቀቅ ወደ ስራ መገባቱን አስረድተዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በምላሻቸው ከዳሰሱዋቸው ጉዳዮች መካከል ከመሰረተ ልማት እና ከተቋማት አገልግሎትና ተደራሽት ጋር የተያያዘም ይገኝበታል፡፡



የክልሉ መንግስት ከተቋማት አገልግሎት እና ተደራሽነት ጋር በተያያዘ በየደረጃው ያሉ ችግሮችን ለመፍታት እየሠራ መሆኑን የተናገሩት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም ከፌዴራል ተቋማትና ሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ያሉ የመሰረተ ልማትና የአገልግሎት ችግሮችን ደረጃ በደረጃ ለመፍታት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል።
በክልሉ በርካታ የገጠር ቀበሌያት የመብራት አገልግሎት በማግኘት ላይ አለመሆናቸውን ገልፀዉ፤ ከመብራትና ቴሌኮም ጋር ተያይዞ ከተደራሽነት አኳያ የሚነሱ ቅሬታዎችን ለመፍታት ከኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል አገልግሎት እና ኢትዮ ቴሌኮም ጋር በቅንጅት በመስራት ችግሩን ለመፍታት ጥረት በመደረግ ላይ መሆኑን አስረድተዋል።


ከዚህ በተጨማሪ አማራጭ የኃይል ቴክኖሎጂዎች ተደራሽነት ላይ ከተለያዩ አለም አቀፍና ሀገር አቀፍ ባለድርሻ አካላት ጋር በጋራ በመስራት የገጠሩን ማህበረሰብ የታዳሽ ኃይል አገልግሎት ተጠቃሚ ለማድረግ ውጤታማ ስራዎች በመሰራት ላይ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
ከንጹሁ የመጠጥ ውሃ ሽፍን ጋር በተያያዘም በበጀት ዓመቱ በርካታ ፕሮጀክቶች በማጠናቀቅ በሚሊዮን የሚቆጠሩ ዜጎችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ በቀጣይም ተጠናክሮ የምቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡
የክልሉ መንግስት የህዝብ ለህዝብ ትስስርን በማጠናከር እና ህዝቡን የሰላሙ ባለቤት በማድረግ ውጤታማ የፀጥታ ስራዎች እየሰራ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ የክልሉን ሰላም ለማደፍረስ የሚሞክሩ ግጭት ጠማቂ አካላትን መንግስት እንደማይታገስ አረጋግጠዋል፡፡



ከማህበራዊ ዘርፍ አኳያ የወባ በሽታ የመከላከል፣ የጤና መድህን ስራ ተደራሽ የማድረግና የጤና ተቋማትን የማጠናከር ስራ ከመዋቅሮች እንደሚጠበቅ አፅኖት ሰጥተዋል።
የትምህርት ለትውልድ ንቅናቄን በማጠናከር ትምህርት ላይ የሚስተዋሉ ችግሮችን ለመቅረፍ የሁሉም ርብርብ እና ድጋፍ እንደሚያስፈልግም ተናግረዋል።
ገቢ ላይ የተሻለ አፈፃፃም የተገኘው ተቀናጅተን በመስራታችን ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ በሁሉም ተግባር በመደጋገፍ ክልሉን የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ መትጋት ይገባናል በማለት ምላሻቸውን አጠቃለዋል።



በጉባኤው ከክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ ጥያቄዎች የአስፈፃሚ ተቋማት ኃላፊዎች ከምክር ቤት አባላት ለተነሱ ምላሽና ማብራሪያ ሰጥተዋል፡፡
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የዲላ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ግብርና ቢር ኃላፊ መሪሁን ፍቅሩ (ዶ/ር)፤ ቢሮው የሚታረስ መሬት በመጨመርና የቴክኖሎጂ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ ባከናወነው ስራ ውጤት ተመዝግቧል ብለዋል።

ከአምናው አንፃር የታረሰ መሬትም ሆነ የቴክኖሎጂ አጠቃቀም በማደጉ ምርታማነት እየተሻሻለ መምጣቱንም የቢሮው ኃላፊ አመላክተዋል።
በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የወላይታ ሶዶ ክላስተር አስተባባሪና የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ በበኩላቸው፤ የክልሉን ገቢ አሟጦ መሠብሰብ ከተቻለ ለሚነሱ የልማት ጥያቄዎች ምላሽ መስጠት እንደሚቻል አረጋግጠዋል።

የክልሉ መንግስት ለታችኛው መዋቅር የፀደቀውን በጀት ሙሉ ለሙሉ ማስተላለፉን የገለፁት ኃላፊው፤ በአግባቡ ከማስተዳደር አንጻር በመዋቅሮቹ ላይ የሚስተዋለው ውስንነት ማረም እንደሚገባም አስገንዝበዋል።
የተለያዩ ኢንሼቲቦችን ከመተግበር አንፃር በመዋቅሮች መካከል የተለያየ አፈፃፀም መኖሩን የጠቆሙት ኃላፊው ለውጤታማነቱ የምክር ቤት አባላት በልዩ ሁኔታ ሊደግፉ እንደሚገባም አብራርተዋል።
የክልሉ ጤና ቢሮ ኃላፊ አቶ እንዳሻው ሽብሩ በበኩላቸው፤ ከጤና ዘርፍ አኳያ በተጠናቀቀው በጀት አመት አዲስ የጤና ተቋማት ግንባታ እንዳይጀመር በማድረግ የተጀመሩትን ለማጠናቀቅ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሰራ እንደሚገኝ ገልፀዋል።

ግንባታ ጀምረው ሳያጠናቅቁ የሄዱ ኮንትራክተሮችን በመለየት በድጋሚ ጨረታ በማውጣት ለሌላ ኮንትራክተር የማሸጋገር ስራ መከናወኑንም ኃላፊው አብራርተዋል።
በክልሉ 26 ከፍተኛ የሆነ የወባ ጫና ያለባቸው ወረዳዎች መኖራቸውን የገለፁት የቢሮው ኃላፊ ባለፉት 3 ወራት የበሽታው ጫና 14 በመቶ መጨመሩን ጠቅሰው የመከላከሉ ስራ አፅንኦት ተሰጥቶ እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል።
የክልሉ መስኖና ቆላማ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኤካል ነትር በበኩላቸው፤ የወይቦ መስኖ ግንባታ በፌደራል መንግስት የተጀመረ ቢሆንም መዘግየቱን ገልፀው ግንባታው እንዲጠናቀቅ ከአከባቢው ለሚነሱ አርሶ አደሮች 110 ሚሊዮን ብር የካሳ ክፍያ እየፈፀሙ እንደሚገኝ ተናግረው ይህ እንደተጠናቀቀ የግንባታ ሂደቱ እንደሚቀጥል አመላክተዋል።

የክልሉ መንግስት 1.3 ቢሊዮን ብር በሚፈጅ ወጪ የመስኖ ፕሮጀክቶች ግንባታ እያከናወነ እንደሚገኝ ገልፀው አብዛኛዎች ፕሮጀክት እየተጠናቀቁ እንደሚገኝም አብራርተዋል።
የክልሉ ትራንስፖርትና መንገድ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ተወልደ ተስፋዬ በተጠናቀቀው በጀት አመት 18 የመንገድና ድልድይ ፕሮጀክቶች እንዲሁም 16 የተጀመሩ ተንጠልጣይ ድልድዮችን ግንባታ የመጨረስ ስራ ተሰርቷል ብለዋል።

ከህብረተሰቡ ፍላጎት አንፃር ሰፊ ስራ እንደሚጠበቅ የገለፁት የቢሮው ኃላፊ የተጀመሩ ፕሮጀክቶችን ፈጥኖ የማጠናቀቅ ስራ በልዩ ትኩረት እንደሚሰራም ገልፀዋል።
በክልሉ በህብረተሰብ ተሳትፎ እየተገዙ የሚገኙ ማሽነሪዎችና ተሽከርካሪዎች በክልሉ በቀጣይ ለሚሰሩ የመንገድ ግንባታ ስራዎች አጋዥ እንደሚሆኑን ኃላፊው ተናግረዋል።
የክልሉ ከተማና መሠረተ ልማት ቢሮ ኃላፊ አቶ ብርሃኑ ዘውዴ በበኩላቸው፤ በክልሉ በሚገኙ ከተሞች የቤት ልማት ተግባርን በተቀናጀ መልኩ እንዲመራ በማድረግ ችግሩን ለመቅረፍ እየተሰራ ነው ብለዋል።

በከተሞች የፈርጅ ለውጦች ከተደረጉ በኃላ ተስፋ ሰጪ እንቅስቃሴዎች እየተስተዋሉ መሆኑን የገለፁት ኃላፊው፤ የከተሞችን የገቢ ምንጭን በማስፋትና ህብረተሰቡን በማስተባበር የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ መትጋት ይገባል ብለዋል። የከተሞችን የዕድገት ሁኔታ ለማመጣጠን ቢሮው የተቀናጀ ድጋፍ እንደሚያደርግም ገልፀዋል።
የክልሉ ስራና ክህሎት ቢሮ ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ማሄ ቦዳ በክልሉ ለሚገኙ ስራ አጥ ወጣቶች የስራ ዕድል ከመፍጠር ባሻገር ብድር እንዲያገኙ የማድረግ ስራዎች እየተከናወነ እንደሚገኝ አብራርተዋል።
በመጨረሻም የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት፤ በ6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን በ7ኛ መደበኛ ጉባዔው፤ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት በሙሉ ድምፅ አፅቋድል፡፡





