“በ2019 በጀት ዓመት የክልሉን ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት የሚያረጋግጡ የዘላቂ ልማት ተግባራት ተጠናክረው ይቀጥላሉ” -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ሕዝብ ምክር ቤት 6ኛ ዙር 5ኛ ዓመት የስራ ዘመን 7ኛ መደበኛ ጉባኤ ሁለተኛ ቀን ቀጥሎ በአርባ ምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በጉባኤው ሁለተኛ ቀን የክልሉን መንግስት የ2019 ጠቋሚ ዕቅድ አቅርበዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት ባለፈው የ2018 በጀት ዓመት፤ የክልሉን ህዝብ በማስተባበር ፍትሃዊ ተጠቀሚነቱን የሚያረጋግጡ እና ክልላዊ የሰላም፤ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት ራዕይን ወደ ላቀ ደረጃ ያሸጋገሩ አመርቂ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉን ጠቅሰው፤ ይሄው በ2019 የመረጠንን ህዝብ የሰጠንን ሀደራ ዞተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም በ2019 ክልላዊና ሀገራዊ ነባራዊ ሁኔታን እና የክልሉን ፀጋና እምቅ የመልማት አቅም ታሳቢ ያደረገ፤ በውጤት የሚለካ መሪ የልማት ዕቅድን በኢኮኖሚና በማህበራዊ ዘርፎች መዋቅራዊ ለውጥ ከሚያመጡ ሀገራዊ ኢኒሼቲቮች ጋር አቀናጅቶ በመፈጸም ለስኬቱ ርብርብ የሚደረግ መሆኑን ተናግረዋል፡፡  

በተለይ የብዝኃ ዘርፍ የኢኮኖሚ ሪፎርሙ የፈጠረውን ምቹ ዕድል ተጠቅሞ በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን በመግለጥ በከተማም ሆነ በገጠር በሁሉም ዘርፍ አሳታፊና አካታች የኢኮኖሚ ግንባታን እውን በማድረግ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገትንና ዘላቂ ልማትን ለማረጋገጥ በትኩረት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ምርታማነትን በላቀ ደረጃ በማሳደግ ተረጂነትን ታሪክ የማድረግ ጉዞን አጠናክሮ የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ተግባራት እና ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ስራዎች በ2019 የበጀት ዓመትም ከክልሉ መንግስት ቀዳሚ የትኩረት አቅጣጫዎች ዋነኛው መሆኑንም ጠቅሰዋል፡፡  

በዚህ ረገድ ለግብርናው ዘርፍ ምርታማነት ልዩ ትኩረት በመስጠት፤ የተጀመሩ ስራዎችን አጠናክሮ በክልሉ ያሉ የመልማት አቅሞችና ፀጋዎች በአግባቡ መጠቀም የሚያስችል እና በቴክኖሎጂ አጠቃቀም የታገዘ ግብርናን አቅዶ በመተግበር ምርትና ምርታማነትን ለማላቅ የሚሰራ መሆኑን አብራርተዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በ2018 በገቢ ዘርፍ የመተዘገበውን ስኬት በማላቅ፤ ወጪን በራስ አቅም ከመሸፈን ባለፈ የውስጥ አቅምን በማጎልበት ለህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎች ብቃት ያለው ምላሽ ለመስጠት በ2019 የበጀት ዓመትም ለገቢ አሰባሰብ ስራ ልዩ ትኩረት በመስጠት የሚሰራ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለዚህም ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሃዊ ገቢን በአግባቡ ከመሰብሰብ ባሻገር በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ ተጨማሪ ሀብት በማፍራትና የገቢ አማራጮችን በማስፋት፣ ከህብረተሰቡ ጋር በመደጋገፍ  ቅድሚያ የሚሰጣቸው የልማት ፕሮጀክቶችን በራስ አቅም በማጠናቀቅ የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ እንደሚሰራ አስረድተዋል፡፡ 

ክልሉ በርካታ ፀጋዎች አሉት ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በበጀት ዓመቱ በየአካባቢው በግብርና፤ በኢንዱስትሪ፤ በቱሪዝም፤ በማዕድንና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ አቅሞችን ተጠቅሞ ከየዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ እንዲሁም ለዜጎች ሰፊ የስራ ዕድል ለመፍጠር በትኩረት የሚሰራ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡

በ2019 የክልሉን መንግስት ተቋማዊ የመፈፀም አቅም የሚያጠናክሩ ስራዎችን በመስራት እንዲሁም የመሶብ የአንድ መስኮት አገልግሎት አሰጣጥን ጨምሮ በየደረጃው የተቋማት አገልግሎት አሰጣጥን በዲጂታላይዜሽን በማዘመን ዘርፈ ብዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ለመቅረፍ የሚሰራ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በበጀት ዓመቱ ልዩ ትኩረት ከሚሰጣቸው ተግባራት መካከል የክልሉ መገለጫ የሆነው ሰላም ዋነኛው መሆኑንም ጠቅሰው፤ በ2019 በክልሉ ማስፈን የተቻለን አንጻራዊ ሰላም፤ በህዝቡ ባለቤትነት በማፅናት የክልሉን ሰላምና ፀጥታ አስተማማኝ ደረጃ ማድረስ ቀዳሚ ትኩረት ሆኖ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

ለሀገራዊና ክልላዊ የብልፅግና ትልም ስኬት የጎላ ፋይዳ ያላቸው፤ እንደ ሀገር በውጥነት ለማሳካት የታለሙ የልማት ኢኒሼቲቮች ውጤታማ ትግበራም ልዩ ትኩረት ይሰጠዋል ሲሉ አስምረዋል፡፡

በዚህ ረገድ በተጠናቀቀው የ2018 የበጀት ዓመት በመጀመሪያ ምዕራፍ በሦሥት ዞኖች ወደ ትግበራ የገባው የገጠር ኮሪደር ልማት በ2019 በማስፋት፤ የገጠር አከባቢዎችን በመሰረተ ልማት በማስተሳሰር በአርሶና አርብቶ አደሩ ህይወት ትርጉም ያለው ለውጥ በማምጣት የገጠር ሽግግር ለማረጋገጥ ይሰራል ብለዋል፡፡

በተጨማሪም የተጀመሩ የሌማት ትሩፋትና የአረንጓዴ አሻራ ስራዎች፤ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት፤ የትህምርትና ጤና የማህበራዊ ልማት ስራዎች፤ በከተሞች የኮሪደር ልማት ተግባራት፣ የሰው ተኮር ስራ አካል የሆነው የክረምት በጎ ፈቃድ አገልግሎት፣  እንዲሁም በህዝብ ተሳትፎ የመጠጥ ውሃና የመንገድ መሰረተ ልማት ፍትሃዊ ተደራሽነትን ማሳደግ በቀጣይም ትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን አስታውቀዋል፡፡

በአጠቃላይ በ2019 በየዘርፉ የተጀመሩ የልማትና የመልካም አስተዳደር ስራዎችን እና ስትራቴጂካዊ ጠቀሜታ ያላቸው ፕሮጀክቶችን በህብረተሰቡ ባለቤትነት፤ በአመራሩ የተግባርና የአመለካከት አንድነትና ቁርጠኝነት አጠናክሮ ከዳር በማድረስ የክልሉን ሕዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚሰራ መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

Leave a Reply