
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ በወላይታ ሶዶ ማዕከል ግንባታው በመጠናቀቅ ላይ በሚገኘው በክልሉ ቤተ-መንግሥት ቅጥር ግቢ አረንጓዴ አሻራቸውን በማኖር በቅጥር ግቢው የአረንጓዴ ልማት ስራ አስጀምረዋል፡፡



የክልሉ መንግስት ለክልሉ የተቋማት ህንፃ ግንባታ ፕሮጀክቶች በሰጠው ልዩ ትኩረት ግንባታቸው በፍጥነት በመከናነው ላይ ከሚገኙ ፕሮጀክቶች፤ ይሄው በወላይታ ሶዶ ከተማ በግንባታ ላይ የሚገኘው የክልሉ ቤተ-መንግሥት አንዱ ነው፡፡
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ በግንባታ ላይ በሚገኘው የክልሉ ቤተ-መንግሥት ቅጥር ግቢ አሻራቸውን ባኖሩበት ወቅት፤- ወቅቱ በአረንጓዴ አሻራችን ተስፋን በመትከል የተፈጥሮ ሚዛኑን የጠበቀ እና ደህንነቱ የተጠበቀ አካባቢን ለትውልድ ለማውረስ ርብርብ የሚናደርግበት ነው ሲሉ ተናግረዋል፡፡



አረንጓዴ አሻራ እንደ ሀገር በክቡር ጠቅላይ ሚ/ር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አስጀማሪነት ከተጀመረ ጊዜ ጀምሮ የተጎዱ ሥነ-ምህዳሮችን መልሶ እንዳገግሙ ከማድረግ ባለፈ በሁሉም መስክ ምርታማነትን በማሳደግ ሁለንተናዊ ብልፅግናን ለማረጋገጥ የሚያስችል መሠረት በመጣል ላይ የሚገኝ ወሳኝ ኢኒሼቲቭ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡
ከዚህም ባሻገር ለናዳና መሰል የተፈጥሮ አደጋዎች ተጋላጭ የሆነ ሥነ-ምህዳር በሚበዛው ክልላችን፤ በአረንጓዴ አሻራ ችግኝ ተከላና በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ስራዎች ተፈጥሮን መንከባከብ የህልውና ጉዳይ ጭምር መሆኑን መገንዘብ ይገባል ሲሉም አስምረዋል፡፡



በዚህ ረገድ፤ በክልሉ ተራሮችን ከስጋት ቀጠናነት ወደ ሀብት ምንጭነት ለመቀየር በሁሉም ዞኖች የተጀመሩ ጥረቶችን፤ በዘንድሮው የአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብር በማጠናከር ከግብ ለማድረስ ኅብረተሰቡን በነቂስ በማሳተፍ ለተከላ ከተያዘው ዕቅድ በላይ ለማሳካት በትኩረት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡



በአረንጓዴ አሻራ መርሃ ግብሩ ከርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪ በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የክልሉ ፋይናንስ ቢሮ ኃላፊ አቶ ተፈሪ አባተ፣ የወላይታ ሶዶ ከተማ ከንቲባ ወ/ሮ እታገኝ ኃ/ማሪያም የርዕሰ መስተዳድር ፅ/ቤት እና ሌሎች የክልሉ አመራሮች ተገኝተዋል።




