ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዓመታዊ የግብር መክፈያ ወቅትን በማስመልከት መልዕክት አስተላለፉ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ዓመታዊ የግብር መክፈያ ወቅትን በማስመልከት መልዕክት ያስተላለፉ ሲሆን፥ የመልዕክቱ ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-

“የክልሉ መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የክልሉን ህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎች በራስ አቅም በብቃት በመመለስ ፍትሀዊ ተጠቃሚነቱን ከማረጋገጥ ባሻገር፤ ለክልላዊና ሀገራዊ የዘላቂ ልማትና የሁለንተናዊ ብልጽግና ግብ ስኬት ለገቢ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።

ግብርን በወቅቱ በታማኝነት መክፈል የዜግነት ግዴታ ብቻ ሳይሆን ሀገርን የመውደድና የማልማት ብሎም የተሻለ ሀገር በመገንባት ለትውልድ የማሻገር ኃላፊነት የተሞላው አኩሪ የዜግነት ተግባር መሆኑንም መገንዘብ ይገባል፡፡

ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን ግብር በአግባቡ መክፈሉ፥ የውስጥ አቅምን በማጎልበት በራስ አቅም የልማት ፍላጎትን ከማሟላት ባሻገር በህብረት የሀገርን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት እና ሁለንተናዊ ብልፅግና የማረጋገጥ ግብን ዕውን የማድረግ ታላቅ የአርበኝነት ተግባር ይፈጽማል፡፡  

በሌላ በኩል ግብርን በመሰወር ለመበልፀግ መሞከር ከሕግ ተጠያቂነትም ሆነ ከህሊና ዕዳ ነፃ የማያደርግ በመሆኑ ግብር ከፋዩ ህብረተሰብ የሚጠበቅበትን ፍትሃዊ ግብር በወቅቱ በታማኝነት በመክፈል የልማት አርበኛነቱን እና የሀገር አለኝታነቱን ዳግም በተግባር በማረጋገጥ ኃላፊነቱን እንዲወጣ ጥሪ እያቀረብኩ፤ የክልሉ መንግስት ታማኝ ግንባር ቀደም ግብር ከፋዮችን የሚያበረታታ መሆኑን ለማሳወቅ እወዳለሁ፡፡

በዚህ አጋጣሚ የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በብቃትና በጥራት በመመለስ ጠንካራ ክልል እና የበለፀገ ህብረተሰብ ለመፍጠር ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በተቀናጀ አግባብ አሟጦ በመሰበሰብና በራስ አቅም የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ በመስራት በጋራ ለሰነቅነው ክልላችንን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልፅግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ ስኬት ሁሉም የድርሻውን እንዲወጣ ጥሪ አቀርባለሁ።

የገቢ ጉዳይ ለአንድ ወገን ተለይቶ የሚሰጥ ተግባር ባለመሆኑም አመራሩ፣ ባለሙያው፤ ማህበራዊ ተቋማትና ሌሎችም ባለድርሻ አካላት ለግብር ዘመኑ የገቢ አሰባሰብ ሥራ ስኬታማነት በጋራ የተቀናጀ ርብርብ እንድታደርጉ ከአደራ ጭምር አሳስባለሁ”።  

ሁለንተናዊ ብልፅግናችንን በጋራ ጥረትና ትጋት እናረጋግጣለን!!

ፈጣሪ ሀገራችንንና ሕዝቦቿን ይባርክ!

ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር

Leave a Reply