
በርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ሰብሳቢነት የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ምክር ቤት በወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በመምከር ቀጣይ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል።


ምክር ቤቱ ወቅታዊ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎች፣ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን ከማስጠበቅ አኳያ በአደጋ ስጋት ስራ አመራር በተሰሩ ስራዎች እንዲሁም በተለያዩ ጊዜያት ለአደጋ በተጋለጡ አካባቢዎች የተከናወኑ የመልሶ ማቋቋም ስራዎች በተመለከቱ አጀንዳዎች ላይ ተወያይቷል።
ምክር ቤቱ በመጀመሪያ አጀንዳው ወቅታዊ የቅደመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በተመለከተ በተለይ በክልሉ ከበልግ ወቅት ጋር ተያያዥ በሆኑ የምርታማነት እና ተያያዥ የህብረተሰብ ጤና ጉዳዮች ዙሪያ መክሯል።


ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ በክልሉ 50 በመቶ የምግብ ዋስትና የሚወሰነው በበልግ ወቅት ምርታማነት መሆኑን ገልፀው፤ በዘንድሮ ዓመት የበልግ ዝናብ ቀድሞ መጥቶ ያለጊዜው ከመውጣቱ ጋር ተያይዞ የደረሱ ዓመታዊ ሰብሎች በተለይም የበቆሎ ሰብል ላይ በተወሰነ ደረጃ ጉዳት ማጋጠሙን ተናግረዋል።
የአየር ንብረት ለውጥ በአለም ደረጃ ከፍተኛ ጉዳት እያስከተለ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በተለይ በበልግ ወቅት በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ካገጠመ የዝናብ ዕጥረት ጋር በተያያዘ ሊከሰቱ የሚችሉ ችግሮችን እንደ ምቹ አጋጣሚ በመጠቀም የምፍትሄ ስራዎች ላይ ማተኮር እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
በዚህ ረገድ ከአጭር ጊዜ አኳያ አርሶ አደሩ ለምርት በመድረስ ላይ እያሉ የዝናብ ዕጥረት የገጠማቸውን ሰብሎች ከማሳ በማንሳት ለከብቶች መኖ ማዋል እንደሚገባ ጠቁመው፤ በመኽር አዝመራ በአጭር ጊዜ ሊደርሱ ለሚችሉ ሰብሎች ትኩረት ሰጥቶ መስራትን ጨምሮ ተያያዥ አፋጣኝ መፍትሄዎች መወሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።


በተጨማሪም ችግሮችን ቀድሞ ለመከላከል በተከታታይ የተመዘገቡ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ስኬት የሚያጠናክሩ ተግባራትን በማጠናከርና ከተረጂነት ዕሳቤ የተላቀቀ ስነልቦና በመገንባት እንዲሁም በተቋማት መካከል ያለውን ቅንጅታዊ አሰራር በማጠናከር በአግባቡ መምራት እንደሚያስፈልግ ገልፀዋል።
በተያያዘ በበልግ ካጋጠመ የአየር ፀባይ ለውጥ ጋር ተያይዞ በአንዳንድ አካባቢዎች የወባ ወረርሽኝ ምልክቶች እየታዩ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ምልክቱ በታየባቸው አካባቢዎች በሽታው እናቶችና ህፃናትን ጨምሮ ህብረተሰቡ ላይ ጉዳት እንዳያደርስ ለመከላከል ሰራዎች ልዩ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባም በአጽንኦት ተናግረዋል።
ምክር ቤቱ በሁለተኛ አጀንዳው የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ከተረጂነት ለመላቀቅና የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን በአደጋ ስጋት ምክር ቤት እየተሰሩ ባሉ ስራዎች ዙሪያ ተወያይቷል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር በማጠናከር ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም ለመሸፈን የተያዘውን ግብ ከማሳካት ባለፈ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን እና የማስፈጸሚያ ስልቶች በሙሉ አቅም ገቢራዊ በማድረግ ማሳካት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
በተለይ ለዚሁ ስኬት የተቀመጡ አምስት ስልቶችን፡- መግባባት፣ ማጥራት፣ ማዘጋጀት፣ ማቀናጀት እና ማሰራጨት በቁርጠኝነት በመተግበር በቅርቡ እንደ ሀገር ለሚታወጀው የምግብ ሉዓላዊነት ግብ ስኬት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።
ርዕሰ መስተዳድሩ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር ለማጠናከር የምርታማነት መጠንን ማሳደግ፣ የመጠባበቂያ እህል ክምችት ተግባራትን ማጎልበት እና የምርት ማከማቻ መጋዘኖች ግንባታን የማጠናከር ስራዎችን በልዩ ትኩረት መስራት እንደሚገባ አስገንዝበዋል።
ምክር ቤቱ በመጨረሻ አጀንዳው በክልሉ በተለያዩ ጊዜያት በደረሱ አደጋዎች የተፈናቀሉ ዜጎችን መልሶ በማቋቋም ተግባር የቤቶች ግንባታ ሥራዎች የሚገኙበት ደረጃን፣ እንዲሁም የኦቶና ሆስፒታል መልሶ ግንባታ እና የዳሰነች መልሶ ማቋቋም የተመለከቱ ጉዳዮች ላይ መክሯል።
ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ በተፈጥሮ አደጋ ጉዳት የደረሰባቸው ወገኖችን መልሶ በዘላቂነት ለማቋቋም እየተከናወነ የሚገኘው ስራ አበረታች መሆኑን ተናግረው፤ ተጎጂዎችን መልሶ በማቋቋም ኑሮ በጀመሩባቸው አካባቢዎች የማህበራዊ መስጫ ተቋማት ተደራሽነት እና የስራ ዕድል ፈጣራ ስራዎች ትኩረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ ገልፀዋል።


ከኦቶና (የወላይታ ሶዶ ዩኒቨርሲቲ ጤና ሳይንስና ሕክምና ኮሌጅ ኮምፕርሄንሲቭ ስፔሻላይዝድ ሆስፒታል) ጋር በተያያዘም የክልሉ መንግስት ለሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ ቀጥተኛ ድጋፍ ከማድረግ ባሻገር ሀብት በማሰባሰብና በመልሶ ግንባታ ተግባራት ዙሪያ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት ሲሰራ መቆየቱን ተናግረዋል፡፡
በዚህ ረገድ የክልሉ መንግስት ለሆስፒታሉ ግንባታ የወሰነውን የ100 ሚሊዮን ብር የገንዘብ ድጋፍ ጨምሮ ዝግ የባንክ ሂሳብ በመክፈት ሀብት በማሰባሰቡ ስራ ከግለሰቦች መሰብሰብ የተቻለውን ገንዘብ በቀጥታ ዩንቨርሲቲው ወደ ከፈተው አካውንት ማስተላለፉን ገልፀዋል፡፡
አሁን ላይ ሆስፒታሉን የሚያስተዳድረው የወላይታ ሶዶ ዩንቨርሲት የሆስፒታሉን መልሶ ግንባታ ለማከናወን ዝግጅት በማጠናቀቅ ላይ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ህብረተሰቡ ለሆስፒታሉ ግንባታ የሚያደርገውን ድጋፍ ማጠናከር እንደሚገባው ተናግረዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ የክልሉ መንግስት በቀጣይም የሆስፒታሉ መልሶ ግንባታ ከዳር እስክደርስ ከባለድርሻ አካላት ጋር በመቀናጀት የሚያደርገውን ድጋፍ አጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አስታውቀዋል፡፡




