
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት 7ኛ መደበኛ ጉባኤ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርት ባቀረቡብት ወቅት፤ በበጀት ዓመቱ የገጠሩን ህብረተሰብ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ከተከናወነ ተግባራት የገጠር ኮሪደር ልማት ወደ ትግበራ መግባቱ ተጠቃሽ መሆኑን ገልፀዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ሀገራዊው የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭ፤ የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለማዘመን እና በተቀናጀ የገጠር ልማት የታለመውን የገጠር ሽግግር ዕውን በማድረግ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ ወደ ትግበራ መግባቱንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ ትግበራ- በወላይታ ዞን፤ በጋሞ ዞን እና በጌዴኦ ዞን የኮሪደር ልማቱ አካል ለሆነው ሞዴል የገጠር መንደር ግንባታ ትኩረት በመስጠት ወደ ስራ መገባቱንም ገልፀዋው፤ በጋሞ ዞን በምዕራብ አባያ ወረዳ ሃመሳ ኢልሎ ሞደል መንደር ከነሙሉ የገጠር ፓኬጆች ተጠናቆ ነዋሪዎች መኖር መጀመራቸውን አስታውቀዋል፡፡



ልማቱ የገጠር አካባቢዎችን በዘመናዊ መሠረተ ልማት በማስተሳሰር የገጠሩን ማኅበረሰብ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ገጠሩን ወደ ልማት ማዕከልነት በማሸጋገር ወደ ዘመናዊ የብልጽግና መሠረትነት የመቀየር ትልምን ያነገበ መሆኑንም ጠቁመዋል፡፡
በአስፈላጊው መሠረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተሳስረው የሚገነቡ ሞዴል መንደሮች፤ የገጠሩ ማኅበረሰብ ባህልና ወጉን ጠብቆ ክብር ያለው ኑሮ እንዲኖር የሚያስችሉ ከመሆኑም በላይ የገጠር ሽግግር ማዕከላት በመሆን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚደረግ ጉዞን የሚያሳልጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡



የኮሪደር ልማቱ ከስራ ዕድል ፈጠራ እና ከቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያም አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ለቤት ግንባታ የአፈር ጡብ በማምረት መጠቀም መቻሉና ለወጣቶች በጡብ ማምረት፤ በግብዓት አቅርቦትና በቤት ግንባታ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በክልሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ የገጠር ኮሪደር ልማት የተገኘው አመርቂ ስኬት፤ የገጠሩን ማኅብረሰብ ኑሮ ለማዘመን በቁርጠኝነት ከተሰራ ባጠረ ጊዜ፣ በውስን ቦታና ሀብት የገጠሩን አካባቢ ማዘመንና መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም ሌሎች ዞኖች ይህን ተሞክሮ ማስፋት የሚገባቸው መሆኑ አስምረዋል፡፡




