በክልሉ በ 2018 የበጀት ዓመት ለ 214 ሺ 656 ዜጎች ቋሚ የስራ ዕድል መፍጠር ተችሏል -ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ምክር ቤት፣ 6ኛ ዙር፣ 5ኛ ዓመት፣ 7ተኛ መደበኛ ጉባኤ ባቀረቡት የ2018 በጀት ዓመት አፈጻጸም ሪፖርት፤ የክልሉ መንግስት ከስራ ዕድል ፈጠራ አኳያ በተለይ የወጣቱን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ለክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት ሰጥቶ መስራቱን ገልፀዋል፡፡

በክልሉ በተለያዩ መስኮች ያሉ ፀጋዎችን ተጠቅሞ የስራ ዕድሎችን የመፍጠር፤ የክህሎትና የአቅም ግንባታ የስልጠና ዕድሎች፤ የብድር፤ የማምረቻና የመሸጫ ቦታዎችን የማመቻቸት፤ የገበያ ትስስር የመፍጠር እንዲሁም በሀገር ውስጥና በውጭ ሀገራት የስራ ስምሪት ዜጎችን ተጠቃሚ የማድረግ ውጤታማ ተግባራት መከናወናቸው ተመላክቷል፡፡  

በዚህም በበጀት ዓመቱ በአጠቃላይ 315,532 የሥራ ዕድል መፈጠሩን በመጥቀስ ከተፈጠረው የሥራ ዕድል ውስጥ 214,656ቱ ቋሚ የሥራ ዕድሎች መሆቸውን አመልክተዋል፡፡

ሴቶች፣ ወጣቶችና አካል ጉዳተኞችን ያካተተው ይህ ስምሪት በግብርና፣ በኢንዱስትሪ፣ በአገልግሎትና በከተማ ኮሪደር ልማት በተደረገው ርብርብ የተገኘ ውጤት ሲሆን፣ ለወጣቶች የተደረገው የመሬት፣ የሼድ፣ የማምረቻና መሸጫ ቦታዎች አቅርቦት እንዲሁም የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ለስኬቱ ከፍተኛ አስተዋጽኦ ማበርከታቸው ተጠቅሷል።

ርዕሰ መስተዳድሩ የተፈጠሩትን የሥራ ዕድሎች በዕውቀት ለመደገፍ 110,890 ዜጎች አጫጭር ሥልጠናዎች ተሰጥተዋል። 46,190 ሰልጣኞችን በመደበኛ መርሃግብር ማሰልጠን እንደተቻለም አመልክተዋል፡፡

አገልግሎትን በቴክኖሎጂ ከማዘመን አኳያ በኢትዮጵያ የሥራ ገበያ መረጃ ሥርዓት (E-LMIS) 153,113 ወጣቶችን መመዝገብ የተቻለ ሲሆን፣ በቀጣይም የማንዋል ምዝገባን ሙሉ በሙሉ በዲጂታል አሰራር ለመተካት መታቀዱን ገልጸዋል።

በሌላ በኩል፣ የሠራተኛና አሠሪ ግንኙነትን ጤናማ ለማድረግ በተሰራው ሥራ ለ51 ኤጀንሲዎች የሥራ ፈቃድ መታደሱንና የቁጥጥር ተግባራት መከናወናቸውን ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው አንስተዋል።

ከስደት ተመላሽ ከሆኑ 251 ዜጎች መካከል 186ቱን ቋሚ የሥራ ዕድል ባለቤት ማድረግ የተቻለ ሲሆን፣ ሕገ-ወጥ የሰዎች ዝውውርን ለመግታት ከአራት ዩኒቨርሲቲዎች ጋር የተካሄደው ጥናት መጠናቀቁንም አብራርተዋል።

በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ 35,400 በላይ ዜጎች በሕጋዊ የውጭ ሀገር ሥራ ስምሪት ተጠቃሚ መሆናቸውን አስረድተዋል።

Leave a Reply