
በርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ(ዶ/ር)፥ ሰብሳቢነት የክልሉ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት መደበኛ ስብሰባውን በርዕሰ መስተዳድር ጽ/ቤት አካሂዷል።
በስብሰባው በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማብሰር የተጀመሩ ስራዎችን ጨምሮ ሌሎች በምክር ቤቱ የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት ቀርቦ ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ እንደ ሀገር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት ለመሸጋገር የተጀመሩ ስራዎች እንዲሁም አጠቃላይ የምክር ቤቱ ተግባራትን ከወትሮ በተለየ፤ በጊዜ የለንም መንፈስ ማከናወን እንደሚገባ ተናግረዋል።
ኢኒሼቲቮችን የምንፈፅምበትን አግባብ በማሻሻል በተለይ በሌማት ቱሩፋት እና በሌሎች የተሻለ አፈፃፀም ለማስመዝገብ መስራት አስፈላጊ መሆኑንም በአጽንኦት ገልፀዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በክልሉ ተጨማሪ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ እና በአመራሩ ቁርጠኛ አመራር በአግባቡ በመምራት ለውጤት ለማብቃት መስራት የሚገባ መሆኑንም አስገንዝበዋል።
ከተረጂዎች ልየታ አንጻር የሴፍትነት ተጠቃሚዎችን ጨምሮ ድጋፍ የሚሹ ተረጂዎችን ከፋይዳ ጋር በማያያዝ እሰከ ታችኛው መዋቅር የመለየትና በአግባቡ የማጣራት ስራ በአፋጣኝ እንዲጠናቀቅም አቅጣጫ አስቀምጠዋል።


ተፈናቃዮችን ወደ ቀያቸው እና ወደ ተዘጋጀላቸው ቦታ የመመለስ እንዲሁም ለአደጋ ተጋላጭ የሆኑ አካባቢዎች ያሉ የህብረተሰብ ክፍሎችን የመጠበቅና እንደ አስፈላጊነቱ ከአደጋ ቀጠና ውጪ በሆኑ ስፍራዎች በጊዜያዊነት ማስፈር የቅድሚያ ቅድሚያ ተሰጥቶት እንዲሰራም አሳስበዋል።
የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፌንድ በተዘረጋው የህግና የአሰራር ማዕቀፍ መሰረት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ የመሰብሰብና የማስተዳደር ተግባራትን በልዩ ትኩረት መምራት እንደማገባም ርዕሰ መስተዳድሩ በአፅንኦት ገልፀዋል።
ከመጠባበቂያ እህል እና ከዕለት ደራሽ ምግቦች ክምችት ጋር በተያያዘም በየመዋቅሩ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዝኖች መዘጋጀታቸውንና በመጋዝኖች ሳይበላሹ መቆየት የሚችሉ የምግብ እህሎችን በበቂ ሁኔታ መኖራቸውን የማረጋገጥ ተግባራት ይበልጥ ትኩረት የሚያሻቸው መሆኑን አስምረዋል።
በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ከተረጂነት ለመላቀቅ እና በተያዘው ጊዜ ውስጥ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል አቅም በመገንባት ለማብሰር የሚከናወኑ ስራዎችን በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ መስራት የሚገባ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡


ለስኬቱ ተግባራትን በተቋማዊ ማዕቀፍና አሰራር በመምራት እንዲሁም በመቶ ቀን እቅድ አካቶ በመስራት ውጤታማነታቸውን መከታተል ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ለዚህ ከክልላዊው ምክር ቤት እና ዐቢይ ኮሚቴ በተጨማሪ የዞን አስተዳዳሪዎችና የከተማ አስተዳደር ከንቲቦች ተግባራትን በቅርበት በመከታተል በትኩረት መምራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም ቅፅበታዊ የአደጋ ምላሽ ስራዎችን በተለመለከተ ከወቅቱ አንፃር የውሃ የማቀብ ስራዎች፤ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የቅድመ ማስጠንቀቂያ ተግባራትን እንዲሁም ከጤና አንፃር አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት ማድረግ ይገባል ሲሉ በማሳሰብ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል።




