“የትግል ምዕራፋችንን በመቀየር የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን በጥናትና ምርምር በተደገፈ አግባብ በትኩረት መስራት ይገባል” ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) 

የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በመጀመሪያ መደበኛ ስብሰባው በክልሉ የመንግስት እና ፓርቲ የቀጣይ መቶ ቀናት ስራዎች ዕቀድ ዙሪያ በመምከር ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጧል፡፡

በስብሰባው የክልሉ አስፈጻሚ ተቋማትና የፓርቲ ስራዎች የቀጣይ 100 ቀናት ዝርዝር ዕቅድ ቀርቦ ሰፊ ውይይት የተደረገበት ሲሆን፤ ምክር ቤቱ በሁሉም ዘርፍ እምርታን ከማስመዝገብና ምርታማነትን ከማሳደግ፤ በገጠርም በከተማም የህዝቡን ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ እንዲሁም በሀገራዊው ግራንድ ስትራቴጂ  እቅድ አግባብ የዘላቂ ልማትና የሁለንተናዊ ብልጽግና  ዕውን ለማድረግ አቅም ከመፍጠር አንጻር በዝርዝር ገምግሟል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በዚሁ ወቅት፤ እንደ ሀገር የ25 ዓመት የግራንድ ስትራቴጂ ፕላን መዘጋጀቱን ጠቅሰው፤ በክልሉ ዕቅዶችን በሀገራዊው ስትራቴጂ በመቃኘትና አዲስ የትግል ምዕራፋ በመቀየር የህዝብን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት በተጨባጭ ማረጋገጥ የሚያስችሉ የልማት ስራዎችን በጥናትና ምርምር በተደገፈ አግባብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡ 

ለሚታቀዱ ዕቅዶች ስኬት ኃላፊነት የሚሰማው እና ተግባራትን በጥብቅ ዲሲፕሊን የሚመራ፣ ሙስናና ብልሹ አሰራርን የሚፀየፍ አመራር ሆኖ መገኘት እጅግ አስፈላጊ መሆኑንም አስምረዋል፡፡

በተለይ አመራሩ የሚሰጠውን ስራ በጊዜ በተገደበ አግባብ መፍፀም የሚችል፣ ውጤት ተኮር የሆነ፣ ከህዝብ ጋር በመቀራረብና ህዝብን በማስተባበር የሚሰራ፤ መረጃን መሰረተ ባደረገና በጥናትና ምርምር በተደገፈ አግባብ ዕቅድ በማዘጋጀት የህዝብን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የሚተጋ ሊሆን እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው አመራሩ ክልላዊ ነባራዊ ሁኔታን ታሳቢ ባደረገ መልኩ አዳዲስ ኢኒሼቲቮችን በመቅረፅ ከተለምዶዊ አሰራር ወጣ ባለ መንገድ ተግባራትን በመምራት መሬት ማውረድ መቻልና በተቋም ያለውን ባለሙያ በአግባቡ በመጠቀም ለውጥ ማምጣት የሚጠበቅበት መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

በክልሉ ያለውን ሀብት በመጠቀም ዕውቀታችንና ጉልበታችንን አስተባብረን ከሰራን ክልሉን ባጭር ጊዜ ውስጥ የብልጽግና ተምሳሌት ማድረግ እንችላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ያሉ አቅሞችን በመጠቀም በየዘርፉ ተጨባጭ ውጤት ለማስመዝገብ ትኩረት ሊደረግባቸው የሚገቡ ቀጣይ የትኩረት አቅጣጫዎችንም አስቀምጠዋል፡፡

በኢኮኖሚያዊ የዕድገትና የማህበራዊ ልማት ዘርፎች ተጨባጭ ለውጥ በማምጣት የህዝብ ተጠቃሚነትን የሚያረጋግጡ በገጠርም ሆነ በከተማ የሚተገበሩ ሀገራዊ የልማት ኢኒሼቲቮች ትግበራን ማጠናከር፤ ከተሞችን የማዘመን የተጀመሩ የኮሪደር ልማት ስራዎች ማጠናቀቅና የወንዝ ዳርቻ ልማት መጀመር እንዲሁም የተጀመሩ የተቋማት ህንፃ ግንባታዎች ማጠናቀቅ ይገኙበታል፡፡

የኢኮኖሚው መሠረት የሆነው ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን የማላቅ፤ የምርት ክላስተሮችን የመፍጠርና የምግብ ሉዓላዊነትን የማረጋገጥ ተግባራት፤ የሌማት ትሩፋትና የቤተሰብ ብልጽግናን የማረጋገጥ፤ በዘርፉ የስራ ዕድል የመፍጠር እንዲሁም በዘርፉ ሌሎች ኢንሼቲቮችን ቀርጾ መተግበር ትኩረት ሚሰጠው መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

በማህበራዊ ልማት ዘርፍ የትምህርት እና የጤናው ዘርፍ ስራዎች ትኩረት የሚያሻቸው መሆኑን ጠቁመው፤ በተለይ በህብረተሰብ ተሳትፎ የትምህርት ግብዓት የማሟላት፤ የስርዓተ ት/ት የማሻሻል ስራዎች፤ የጤና መድህን ሽፋን የማሳደግ እንዲሁም የውሃ እና የመንገድ ፕሮጀክቶችን በተባለው ጊዜ በማጠናቀቅ ሽፋኑን የማሳደግ ስራዎች የትኩረት መስክ መሆናቸውን ተናግረዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ የውስጥ አቅምን በማጎልበት በራስ አቅም የህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ መስራት የክልሉ መንግስት የትኩረት አቅጣጫ መሆኑንም ጠቅሰዉ፤ በየደረጃው ለገቢ አሰባሰብ ስራ ልዩ ትኩረት በመስጠት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሃዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ የውስጥ አቅምን ማሳደግና አላስፈላጊ ወጪዎችን መቀነስ እንደሚገባም አሳስበዋል፡፡ 

ከስራ ዕድል ፈጣራ አኳያ ዕውቀትና ክህሎት መር የስራ ዕድል ፈጠራ ትኩረት የሚሰጠው መሆኑንም ገልፀው፤ በተለይ በክልሉ በግብርና፤ በቱሪዝም፤ በማዕድን፤ በኢንዱስትሪ እና በተለያዩ የኢንቨስትመንት መስኮች ያሉ እምቅ አቅሞችን ተጠቅሞ ሰፊ የስራ ዕድል በመፍጠር ከዘርፉ የሚገኝ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነትን ለማሳደግ የክልሉን የኢንቨስትመንት ሮድ ማፕ በማዘጋጀት መስራት እንደሚገባ በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

በተጨማሪም የመሬት ሀብትን ከብክነት የመታደግ፣ የሰው ሃይል ድልድልና መረጃ የማጥራት፤ የተቋም ግንባታ ስራዎችን የማጠናከር፤ በህዝቡ ባለቤትነት አስተማማኝ ሰላምን የማፅናት፤ ተደጋጋሚ ግጭቶች በሚከሰትባቸው አካቢዎች ችግሩን ለመለየት ጥናት የማድረግ እንዲሁም ለመንግስት ሰራተኛው በወቅቱ ደሞዝ የመከፈል ጉዳዮች ትኩረት የሚያሻቸው መሆኑን አክለዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ፈጣን ኢኮኖሚያዊ ዕድገት እና ዘላቂ ልማትን በማረጋገጥ የክልሉን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የመንግስት ጥረት ብቻውን በቂ አለመሆኑን ጠቅሰው፤ አልሚ ባለሀብቱና የግሉ ዘርፍ እንዲሁም መላው የክልሉ ህዝብ የልማት ተሳትፎአቸውን ልያጠናክሩ እንደሚገባ በመግለጽ ሃሳባቸውን አጠቃለዋል፡፡

Leave a Reply