የክልሉ መንግስት ለዞን አስተዳደር እርከኖች እና ለሪጅዮ ፖሊስ ከተሞች ለ2019 በጀት አመት 70.6 ቢሊዮን ብር እንዲመደብ ውሳኔ አሳለፈ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ መንግስት የ2019 በጀት ዙሪያ ከዞን አስተዳደር አመራሮች እና ከሪጅዮ ፖሊስ ከተሞች ከንቲባዎች ጋር በአርባምንጭ ከተማ ተወያይተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ የክልሉ መንግስት የ2019 በጀት ዓመት የበጀት ድልድል፤ የክልሉን ሕዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎችና የመልማት ፍላጎቶች ይበልጥ በቅርበት ምላሽ በመስጠት ተደራሽ ማድረግን ታሳቢ ባደረገ መልኩ መሰናዳቱን ገልፀዋል፡፡

በዚህም የበጀት ድልድሉ የክልሉን ድርሻ በእጅጉ በቀነስና የዞኖችን ድርሻ ከፍ ባደረገ መልኩ ከአጠቃላይ በጀቱ ሰማንያ በመቶ (80%) ለዞን አስተዳደር እርከኖችና ለሪጅዮ ፖሊስ ከተሞች ሃያ በመቶ (20%) ለክልል ማዕከላት እንዲሆን መወሰኑን ርዕሰ መስተዳድሩ አስረድተዋል።  

በዚህ መሰረት፤ የክልሉ መንግስት ለዞን አስተዳድር እርከኖች እና ለሪጂዮ ፖሊስ ከተሞች  የ2019 በጀት የውስጥ ገቢን ጨምሮ ፡- 70,592,656,845  (ሰባ ቢሊዮን አምስት መቶ ዘጠና ሁለት ሚሊዮን ስድስት መቶ ሀምሳ ስድስት ሺህ ስምንት መቶ አርባምስት ብር ) እንዲመደብ መወሰኑን አስታውቀዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ የበጀት ድልድሉ የኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ምክር ቤት ለክልሎች ያስተላለፈው ቀመርን መሰረት በማድረግ በመስተዳድር ምክር ቤት ታይቶና ተገምግሞ፤ በክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት የፀደቀው የሀብት ማከፋፈያ ቀመር መሰረት ያደረገ መሆኑን አብራርተዋል፡፡

የበጀት ድልድሉ የክልሉን ሕዝቦች ወንድማማችነት፤ አብሮ የመልማት ትልም እና ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በሚያስችል መልኩ መሰናዳቱንም ጠቅሰው፤ ከአጠቃላይ በጀቱ (56.2%) በውስጥ ገቢ፤ ቀሪው (43.8%) በፌደራል መንግስት ድጎማ የሚሸፈን መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በ2019 የበጀት ዓመት፤ በክልሉ በሁሉም የአስተዳደር እርከኖች ከመቸውም ጊዜ በላይ የውስጥ ገቢን ማሳደግ፤ አላስፈላጊ ወጪን መቀነስ እና ለበጀት አጠቃቀም ከፍተኛ ትኩረት በመስጠት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።

በተለይ የገቢ አሰባሰብ ስራን በተደራጀ እና በተቀናጀ አግባብ በመምራት፤ የገቢ ምንጮችን በማስፋት እና የውስጥ አቅምን በማጎልበት በራስ አቅም የልማት ፕሮጀክቶችን ለመሸፈን በትኩረት መስራት እንደሚገባም በአጽንኦት ተናግረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የዞን አስተዳደር እርከኖች በጀትን ለታለመለት ዓላማ በማዋል እና የመልካም አስተዳደር ጥያቄ የሚያስነሱ የልማት ፕሮጀክቶችን የቅድሚያ ቅድሚያ ሰጥቶ ለማጠናቀቅ በመስራት የህብረተሰቡን ጥያቄዎች መመለስ የሚገባቸው መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡

ከዚህም በላይ ህዝቡን የልማቱ ባለቤት በማድረግ እና በየደረጃው የተለያዩ የህብረተሰብ ክፍሎችን በመደበኛና በንቅናቄ በሚመሩ የልማት ስራዎች በንቃት በማሳተፍ የበጀት ዓመቱን የልማት ስራዎች ዕቅድ ሙሉ በሙሉ ለማሳካት መስራት እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በበጀት አመቱ ምርትና ምርታማነትን በማሳደግ፤ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን በአግባቡ ለይቶ ተጨማሪ ሀብት ለማፍራት በመስራት እና የውስጥ አቅምን በማጎልበት የህዝቡን የልማት ጥያቄዎች በብቃት ለመመለስ በትኩረት መስራት እንደሚገባ በማሳሰብ መድረኩን አጠቃለዋል፡፡

Leave a Reply