“የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ፍትሃዊነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን፣ ከንክኪ የፀዳ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የስራ ውጤታማነትን የሚያሳድግ ነው”  ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በአርባ ምንጭ ከተማ የተገነባውን የክልሉን 2ኛ መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል በይፋ መርቀው አገልግሎት አስጀምረዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በምረቃ ስነስርዓቱ ላይ ባስተላለፉት መልዕክት፤ ማዕከሉ 7ኛው ሀገራዊ ምርጫን እጅግ ሰላማዊ፥ ነፃ፥ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ በሆነ መንገድ በስኬት ባጠናቀቅንበት ማግስት ተመርቆ ለአገልግሎት ዝግጁ መሆኑ ታሪካዊ ያደርገዋል ሲሉ ተናግረዋል።

ሀገራዊ ምርጫው ለዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ አዲስ ምዕራፍ የከፈተ ብቻ ሳይሆን ህዝባችን ለሀገሩ ያለውን አለኝታነት ያረጋገጠበት ጭምር ነው ሲሉም አክለዋል።

ርዕሰ መስተዳድሩ በሀገራዊ ምርጫው በነቂስ የተሳተፈው ህዝብ ዘርፈ ብዙ የልማትና የመልካም አስተዳደር ጥያቄዎችን የመመለስ እና ሀገር የማሻገር ታላቅ ኃላፊነት የጣለ መሆኑንም አውስተዋል። 

በዚህ ረገድ የክልሉ መንግስት ከአገልግሎት አሰጣጥ ጋር የተያያዙ የመልካም አስተዳደር ችግሮችን ፈትሾ በብቃት ለመፍታት ቁርጠኛ መሆኑን ገልፀዋል፡፡

ለዚህ በክልሉ ባጭር ጊዜ ውስጥ ሁለተኛውን መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ ማዕከል በማጠናቀቅ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ መቻሉ አንዱ ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ማዕከሉ በክልሉ ባለፉ ጊዜያት የመልካም አስተዳደር ችግሮች ለመፍታት በተከናወኑ ስራዎች የተመዘገቡ ስኬቶችን ለማላቅ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡ 

በመንግስት ተቋማት የነበሩ የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት በቴክኖሎጂ የታገዘ ፈጣንና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ መዘርጋት አስፈላጊ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ መሶብ በአንድ ማዕከል የተቀናጀ አገልግሎት ለተገልጋዩ መስጠት የሚያስችል መሆኑን አስገንዝበዋል፡፡

ማዕከሉ በቴክኖሎጂ የተደገፈ፤ ዘመናዊና ቀልጣፋ የአገልግሎት አሰጣጥ ስርዓት በመዘርጋት ለተገልጋዩ ህብረተሰብ ጊዜንና ወጪ ቆጣቢ የሆነ ፈጣን አገልግሎት በአንድ ማዕከል ተደራሽ ማድረግ የሚያስችል እና ተጠቃሚነቱን የሚያረጋግጥ መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ ማዕከሉ ዜጎች የተሟላ የዲጂታል አማራጮችን በመጠቀም በቀላሉ የተለያዩ የክልል እና የፌደራል ተቋማት አገልግሎቶችን በአንድ ጣሪያ ስር በማጣመር እንዲያገኙ የሚያስችል መሆኑንም ገልፀዋል።

መሶብ መንግስት ለሰው ተኮር አገልግሎት የሰጠው ትኩረት የተግባር ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ተገልጋዩ ህብረተሰብ ባልተንዛዛ አሰራር የተቀላጠፈ አገልግሎት እንዲያገኝ የሚያስችል መሆኑንም ተናግረዋል።

የአንድ ማዕከል አገልግሎቱ ፍትሃዊነትንና ተጠያቂነትን የሚያሰፍን ሆኖ ከንክኪ የፀዳ በመሆኑ ቀልጣፋ አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር የስራ ውጤታማነትን የሚያሳድግ መሆኑንም ገልፀዋል።

እንደ ሀገር በክቡር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፥ ጠንሳሽነት የተጀመረው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት በሀገራችን የመንግስት የአገልግሎት አሰጣጥ ላይ የታሪክ እጥፋት ማስመዝገብ ያስቻለ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ዘመኑን የዋጀ በቴክኖሎጂ የታገዘ አገልግሎት አቀናጅቶ የያዘው የመሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት፤ የተቋማት የአገልግሎት አሰጣጥ ችግሮችን ከመፍታት በተጨማሪ ለታለመው የዲጂታል ኢትዮጵያ ስኬታማ ጉዞ መዳልድል የሚፈጥር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

በክልሉ የማዕከሉን ዝግጅት ባጭር ጊዜ ውስጥ በማጠናቅቀ ለአገልግሎት ዝግጁ ማድረግ መቻሉ ስራዎች በአግባቡ ከተመሩ ትልቅ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል ያሳየ መሆኑንም ገልፀው፤ ለማዕከሉ በስኬት መጠናቀቅ አስትዋጽኦ ላበረከቱ አካላት ምስጋና አቅርበዋል፡፡

በክልሉ በቀጣይም የተቋማት አገልግሎቶችን የማዘመን ተግባራትን የማጠናከር እና የአንድ ማዕከል አገልግሎትን በማስፋፋት የተቀላጠፈ የመንግስት አገልግሎት አሰጣጥ ተደራሽ የማድረግ ስራዎች ተጠናክረው የሚቀጥሉ መሆኑንም አረጋግጠዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ የዚሁ አካል በቅርቡ የክልሉ 3ኛው መሶብ የአንድ ማዕከል አገልግሎት መስጫ በዲላ ከተማ ተጠናቆ ለአገልግሎት ዝግጁ የሚሆን መሆኑንም አስታውቀው ለአገልግሎቶቹ መጀመር ከፍተኛ አስተዋፅኦ ላበረከቱት አካላት በክልሉ መንግስት ስም ምስጋና አቅርበዋል።

የክልሉ ም/ርዕሰ መስተዳድር እና የመሶብ አንድ ማዕከል ቦርድ ሰብሳቢ አበባየሁ ታደሰ (ዶ/ር) በበኩላቸው በሦስተኛው ዙር በደቡብ ኢትዮጵያ ክልል ከተሞች እና በመቀጠልም በዞን ከተሞች የተጀመረው ይህ የአንድ ማዕከል አገልግሎት ስምሪት ይበልጥ ተጠናክሮ እንዲቀጥል፣ ከዚህ ቀደም ከነበረው በተሻለ መልኩ ክትትልና ጥረት እንደሚደረግ አረጋግጠዋል።

Leave a Reply