
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በበጀት ዓመቱ አጠቃላይ የስራ አፈጻጸም ሪፖርታቸው፤ በማህበራዊ ልማት ዘርፍ በተለይም በትምህርት እና በጤናው ዘርፍ የተመዘገቡ እምርታዊ ውጤቶች በዝርዝር አመላክተዋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ በሪፖርታቸው፤ በትምህርት ዘርፍ በተጠናቀቀው የ2018 የበጀት ዓመት፤ በትምህርት ለትውልድ ንቅናቄ መላዉን ህብረተሰብ በማሳተፍ የት/ቤቶችን ደረጃ በማሻሻል የትምህርት ጥራት እና ተደራሽነትን ለማሳደግ በተሰሩ ስራዎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገልፀዋል፡፡
ህብረተሰቡ በገንዘብ፣ በቁሳቁስ፣ በጉልበት እና በዕውቀት ድጋፍ ማድረጉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም 768 ምሊዮን 640 ሺህ 803 ብር በላይ የሚገመት ሀብት በመሰብሰብ በትምህርት ዘርፍ የተስተዋሉ ክፍተቶችንና የግብዓት ዕጥረት ለመቅረፍ ጥቅም ላይ ማዋል መቻሉን ተናግረዋል፡፡

በትምህርት ስርዓቱ የነበረውን የጥራትና ተገቢነት ችግር ለማሻሻል እና የታዩ ችግሮችን ለመቅረፍ በአዲሱ የትምህርት ፍኖተ-ካርታ መሰረት በየደረጃው መስፈርቱን የሚያሟሉ መምህራንን በማሰልጠንና በመመልመል የማሰማራት፣ አስፈላጊ የትምህርት መርጃ መሣሪዎችንና ቁሳቁሶችን የማሟላት ሥራ መሰራቱንም ገልፀዋል፡፡
የትምህርት ተደራሽነትንና ፍትሃዊነት ከማረጋገጥ አንጻርም ህብረተሰቡንና አጋር አካላትን ያሳተፈ ጥረት በማድረግ፤ የአዳዲስ ትምህርት ቤቶች ግንባታን ጨምሮ ነባሮችን የማጠናከር ውጤታማ ስራ መሰራቱን ዘርዝረዋል፡፡



በዚህ ረገድ በ2018 የትምህርት ዘመን ማህበረሰቡን በማሳተፍ 50 ቅድመ-አንደኛ፣ 23 አንደኛና መካከለኛ እንዲሁም 4 ሁለተኛ ደረጃ አዲስ ትምህርት ቤቶች መገንባት የተቻለ መሆኑ ተመላክቷል፡፡
በተያያዘ ተጨማሪ የመማሪያ ክፍሎችን በማስፋፋቱ ረገድም 233 ቅድመ-አንደኛ፣ 654 አንደኛና መካከለኛ እንዲሁም 151 ሁለተኛ ደረጃ ክፍሎች ሲገነቡ፤ በበጀት ዓመቱ 524 ቅድመ-አንደኛ፣ 1,929 አንደኛና መካከለኛ እንዲሁም 382 ሁለተኛ ደረጃ መማሪያ ክፍሎችን መጠገን መቻሉም ታውቋል፡፡



ርዕሰ መስተዳድሩ በጤናው ዘርፍ በተመሳሳይ የህብረተሰቡን ጥራት ያለው ፍትሃዊ የጤና አገልግሎት ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ በበጀት ዓመቱ በተሰሩ ዘርፈ ብዙ ስራዎች ስኬት መመዝገቡንም በሪፖርቱ አመላክተዋል።
በጤናው ዘርፍ ሁሉን አቀፍ የጤና ኤክስቴንሽን ፓኬጆችን በቤተሰብ ደረጃ በመተግበር 478 ሺህ 354 አባወራና እማወራዎችን ሞዴል ማድረግ መቻሉንም ገልፀዋል።


በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በሰለጠነ ባለሙያ ታግዘዉ የወሊድ አገልግሎት ማግኘት ከሚገባቸው 279 ሺህ 816 እናቶች ዉስጥ 239 ሺህ 602 እናቶች በጤና ተቋማት እንዲወልዱ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል። ይህም ከባለፈው ዓመት ተመሳሳይ ወቅት ጋር ሲነፃፀር መሻሻል የታየበት መሆኑን በሪፖርታቸው አመላክተዋል።
የተቀናጀና ተደራሽ የጤና አገልግሎትን በሁሉም አካባቢዎች ለመተግበር እየተደረገ ያለው ጥረት ከማሳካት አንጻርም፤ በቤተሰብ ዕቅድ አገልግሎት ሽፋን 1 ሚሊዮን 368 ሺህ 930 ሴቶችን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉንም ጠቅሰዋል፡፡



ከዚህ በተጨማሪ በበጀት ዓመቱ 1 ሚሊዮን 18 ሺህ 331 አዲስ የማህበረሰብ አቀፍ የጤና መድህን አባላት ማፍራት መቻሉንም ርዕሰ መስተዳድሩ ገልፀዋል።
በህብረተሰብ ጤና ረገድ፤ በተለይም በተለያየ ወቅት የተከሰቱ ወረርሽኞችና ሌሎች ድንገተኛ አደጋዎች ከመቆጣጠርና ከመከላከል አንጻር፤ በበጀት ዓመቱ ያጋጠመን የወባ እና የማርበርግ ቫይሬስ ወረርሽኝ በተቀናጀ የመከላከልና የመቆጣጠር ተግባር በአጭር ጊዜ ውስጥ መቆጣጠር መቻሉም ተመልክቷል።
በጤና ተቋማት ግንባታ ረገድ በበጀት ዓመቱ፤ 3 የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎችን ማለትም የበቶ፣ የቱርሚ እና የዘፊኔ የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታሎች ግንባታ በማጠናቀቅ አገልግሎት እንዲሰጡ ማድረግ መቻሉን ጠቅሰው፤ የጨለለቅቱን የመጀመሪያ ደረጃ ሆስፒታል ግንባታ ፊዚካል አፈጻጸም 80 ከመቶ ማድረስ መቻሉን ገልፀዋል፡፡
በተጨማሪም በተጠናቀቀው 2018 በጀት ዓመት የሳውላ ደም ባንክ ግንባታ ሥራ ተጠናቅቆ አገልግሎት መስጠት እንዲችል ማድረግ የተቻለ ሲሆን፤ የሶዶ ደም ባንክ ግንባታ ፊዚካል አፈጻጸምን 90 በመቶ ማድረስ መቻሉም ታውቋል።




