
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት ርዕሰ መስተዳድር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር)፤ የኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ትንበያን ተከትሎ በቀጣይ ከሚጠበቅ የዝናብ ሁኔታ ጋር በተያያዘ ወቅታዊ መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ በማህበራዊ ትስስር ገፃቸው ያስተላለፉት መልዕክት ሙሉ ቃል እንደሚከተለው ቀርቧል:-
ዝናብን ለልማት ዕድል እንጠቀም፤ ከተፈጥሮ አደጋም ሕዝባችንን እንጠብቅ!
በኢትዮጵያ ሚቲዎሮሎጂ ኢንስቲትዩት የአየር ትንበያ መረጃ መሠረት፣ በቀጣዮቹ ጊዜያት በክልላችን አብዛኛዎቹ አካባቢዎች ከመደበኛው በላይ ዝናብ ሊኖር እንደሚችል ተጠቁሟል። ይህ ሁኔታ ለክልላችን የልማት ዕድልን ከመፍጠሩም በላይ፣ በአግባቡ ካልተዘጋጀን የተፈጥሮ አደጋ ስጋትንም የሚያሳድግ በመሆኑ ከወዲሁ ተገቢዉን ዝግጅት እና ጥንቃቄ ማድረግ ይጠይቃል።
ዛሬ በተካሄደው የአደጋ ስጋት ሥራ አስፈፃሚ ኮሚቴ ስብሰባ ጉዳዩን በዝርዝር ከተመለከትን በኋላ ቀጣይ የሚሰሩ ተግባራት ተለይተዋል።
ስለሆነም ዝናቡን ወደ ምርታማነት፣ ስጋቱን ወደ ዝግጁነት በመቀየር ለልማት የተፈጠረውን ዕድል በአግባቡ መጠቀምና ሊከሰቱ የሚችሉ አደጋዎችን በቅድሚያ መከላከል የሁላችንም የጋራ ኃላፊነት መሆኑን ማሳሰብ እወዳለሁ።
በመጀመሪያ፣ ዝናቡን ለግብርና ልማትና ለምርታማነት ማሳደግ መጠቀም ይገባል።
በክልላችን የመኸር አምራች አካባቢዎች በዝናብ እጥረት ምክንያት የተስተጓጎሉ የግብርና ሥራዎችን ለማካካስ የሚጠበቀውን ዝናብ በአግባቡ መጠቀም ወሳኝ ነው። በተለይም አሁን የመኸር ወቅት እና እርሻ ላይ የሆኑ አከባቢዎች (ኮንሶ፣ ኮሬ ፣ጋርዱላ፣ቡርጂ እና ሌሎችም ዞኖች አርሶ አደሩና ከፊል አርብቶ አደሩ ከዝናቡ የበለጠ ተጠቃሚ እንዲሆኑ የተቀናጀ የዝግጅትና የድጋፍ ሥራ መሠራት አለበት።
በዚህ ረገድ በየደረጃው የሚገኙ የግብርና ተቋማት፣ አመራሮችና ባለሙያዎች አስፈላጊውን የግብርና ግብዓት፣ የቴክኒክ ድጋፍና የባለሙያ እገዛ በወቅቱ በማቅረብ፣ የእርሻ ዝግጅትን በማፋጠንና የውሃ አጠቃቀምን በማሻሻል ምርታማነትን ለማሳደግ የተቀናጀ ርብርብ እንድታደርጉ አደራ ማለት እፈልጋለሁ።
በሁለተኛ ደረጃ፣ ከዝናብ ጋር ተያይዞ ሊከሰት የሚችልን የተፈጥሮ አደጋ በቅድሚያ መከላከል ላይ ልዩ ትኩረት ሰጥተን መስራት አለብን።
ከመደበኛው በላይ የሚጠበቀው ዝናብ በተለይም ለመሬት መንሸራተት፣ ለጎርፍና ለሌሎች ተያያዥ አደጋዎች ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች ላይ ከፍተኛ ጥንቃቄ የሚጠይቅ ነው። በተለይም በጋሞ፣ በጎፋ፣ በወላይታ፣ በኦሪ፣ በደቡብ አሞ፣ በጌዴኦ ዞኖችና በሌሎች ለተፈጥሮ አደጋ ተጋላጭ በሆኑ ደጋማ አካባቢዎች የቅድመ መከላከል ሥራዎች በልዩ ትኩረት መከናወን አለባቸው።
ለዚህም በሕዝብ ተሳትፎ የተጀመሩ የአደጋ መከላከል ሥራዎችን ማጠናከር፣ ተጋላጭ አካባቢዎችን አስቀድሞ መለየት፣ የቅድመ ማስጠንቀቂያ ሥርዓትን ማጠናከርና አስፈላጊ ሲሆን በአደጋ ስጋት ውስጥ የሚገኙ ወገኖቻችንን ወደ ደህንነታቸው የተጠበቀ አካባቢ በጊዜያዊነት የማዛወር ሥራ በወቅቱ መከናወን ይገባል።
የሰው ሕይወትን ከማዳን የሚበልጥ ቅድሚያ የለም። አደጋ ከተከሰተ በኋላ ምላሽ ከመስጠት ይልቅ አስቀድሞ መከላከል የተሻለ አመራርና ኃላፊነት መገለጫ ነው።
በሦስተኛ ደረጃ፣ የተቋማት ቅንጅትና የሕዝብ ግንዛቤ ማሳደግ ወሳኝ ነው።
በየደረጃው ያሉ የመንግሥት አመራሮች፣ የአደጋ ስጋት አስተዳደር ተቋማት፣ የእምነት ተቋማት፣ የሚዲያና የሕዝብ ግንኙነት አካላት በተቀናጀ መንገድ በመንቀሳቀስ ለሕብረተሰቡ ትክክለኛ፣ ወቅታዊና ተደራሽ የሆነ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃ እንዲደርስ ማድረግ አለባቸው።
በተለይም የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮች በየአካባቢያቸው ያለውን ተጨባጭ ሁኔታ በቅርበት በመከታተልና ሕዝቡን በማሳተፍ ተጨባጭ የመከላከል ሥራዎችን እንዲያከናውኑ አሳስባለሁ።
በተመሳሳይም ለአደጋ ተጋላጭ በሆኑ አካባቢዎች የምትኖሩ የክልላችን ነዋሪዎች የሚሰጡ የቅድመ ማስጠንቀቂያ መረጃዎችን በትኩረት እንድትከታተሉ፣ የመንግሥት አካላት ከሚያከናውኗቸው የአደጋ መከላከል ሥራዎች ጋር በንቃት እንድትተባበሩና የራሳችሁንና የቤተሰቦቻችሁን ደህንነት ለመጠበቅ አስፈላጊውን ጥንቃቄ እንድታደርጉ ጥሪዬን አቀርባለሁ።




