
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልላዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ለማብሰር በክልሉ በመንግስትና ፓርቲ አመራር በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በመከናወን ላይ የሚገኙ የ5ኛ ሳምንት ተግባራት ያሉበት ደረጃን በበይነ መረብ በመገምገም ለታለመው ግብ ስኬት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
በስብሰባው የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር አቶ ወገኔ ቡዙነህ፤ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማብሰር የተከናወኑ ተግባራትን በተለይም የዕለት ደራሽ እና የመጠባበቂያ እህል ክምችት እንዲሁም የአደጋ ጊዜ የመጠባበቂ ፌንድ የተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ በውይይቱ፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት ለመሸጋገር እንደ ሀገር በወጥነት ለማሳካት ለተያዘው ግብ ስኬት፤ በክልሉ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥና የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል አቅም በመገንባት በታህሳስ 2019 በይፋ ለማብሰር በመሰራት ላይ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
ለዚሁ ግብ ስኬት በክልሉ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት የ5ኛው ሳምንት አፈጻጸም አበረታች መሆኑን የገመገሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አመራሩ አጀንዳው የሉዓላዊነት ጥያቄን ያዘለ፤ ከሰው ልጅ ህይወት ጋር የተሳሰረ የህልውና ጉዳይ መሆኑን በውል ተገንዝቦ በቁርጠኝነት መምራት እንደሚገባው በአጽንኦት ገልፀዋል፡፡


ለስራዎች ውጤታማነት ተግባራትን በተቋማዊ ማዕቀፍና አሰራር መምራት መሠረታዊ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ለዚህም በየደረጃው በመንግስትና ፓርቲ የተዘረጉ አደረጃጀቶችን እና የአሰራር ስርዓት ማዕቀፎችን ተጠቅሞ ለተያዘው ግብ ስኬት የተቀናጀ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
በውይይቱ የክልሉ ብልጽግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገ/መስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ በክልሉ በታህሳስ 2019 ዓ/ም ለማወጅ ለታለመው ሰብዓዊ ድግፍ በራስ አቅም የመሸፈን ግብ ስኬት የሚከናወኑ ስራዎች በአደረጃጀት በመመራት ላይ መሆኑን ጠቅሰው፤ መረጃዎችን የማጥራት ስራዎች ትኩረት የሚያሻቸው መሆኑን ተናግረዋል፡፡

ከተረጂነት በመላቀቅ በራስ አቅም ሰብዓዊ ድጋፍን ለመሸፈን በሚደረገው እንቅስቃሴ፤ የሁሉም ባለድርሻ አካላት ቅንጅታዊ አሰራርና ጠንካራ ክትትል አስፈላጊ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ለውጤታማነቱ የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን በአግባቡ ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ ገልፀዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በመጨረሻም በክልሉ ተረጂነትን በማስቀረት የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ለመገንባት በመከናወን ላይ ያሉ ተግባራት የሚያጠናክሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል፡-
ተግባራትን በጠንካራ ተቋማዊ ማዕቀፍ መምራት፡- በክልሉ በፓርቲና መንግስት በተዘረጉ የዐቢይ ኮሚቴ፤ ምክር ቤትና በቴክኒክ ኮሚቴዎች የሚመሩ ተግባራትን ባለቤት ባለው መልኩ ስርዓት ዘርግቶ እስከታችኛው መዋቅር በተቋማዊ ማዕቀፍ መምራት ይገባል፤
ሥራዎችን በጊዜና በሙላት ተጠያቂነት ባለው መልኩ መፈፀም፡- የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል አቅም ለመገንባት የተለዩ ሥራዎችን ተጠያቂነት ባለው አግባብ በመምራት፤ በጊዜና በሙላት በተጨባጭ መረጃ በምታይና በሚለካ መልኩ በመፈጸም ለውጤት ማብቃት ይገባል፤
የሕዝቡን አቅም መጠቀም፡- የዕለት ደራሽና የመጠባበቂያ እህል ክምችት እንዲሁም የአደጋ ጊዜ የመጠባበቂ ፌንድ በማሰባሰቡ ረገድ የህብረተሰቡን የትብብርና የመረዳዳት እሴት በአግባቡ መጠቀም በሚያስችል አግባብ ሕዝብ በማስተባበር፤ በተለይ የበልግ ሰብል ከደረሰባቸው አካባቢዎች በታቀደው ልክ ለማሰበሰብ መስራት ይገባል፤
ከዚህ ጋር በተያያዘ በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፌንድ በተዘረጋው የህግና የአሰራር ማዕቀፍ መሰረት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ መሰብሰብና ማስተዳደር ይገባል፤
ተረጂዎችን ከፋይዳ ጋር በማስተሳሰር መረጃ ማጠናቀር፡- ተረጂዎችን ከብሔራዊ የፋይዳ የዲጂታል መታወቂያ ጋር በማስተሳሰር መረጃዎችን በአግባቡ ማጠናቀር ይገባል፡፡ ተጨማሪ ድጋፍ የሚሹ ዜጎች ካሉም እሰከ ታችኛው መዋቅር በአግባቡ በመለየት ምላሽ መስጠት የሚያስችል ማይክሮ ዕቅድ ማዘጋጀት ያስፈልጋል፡፡


ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም በተያዘው ክረምት በንቅናቄ የሚመሩ ተግባራትን በተለይም በክረምት የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ትርጉም ያለው ስራ የመስራት፤ የሐምሌ 27 የአረንጓዴ አሻራ የአንድ ጀንበር ተከላ ዝግጅት እንዲሁም የገቢ አሰባሰብ ስራዎች የሚያጠናክሩ አቅጣጫዎች አስቀምጠዋል፡፡
በመጨረሻም በየደረጃው ያለው አመራር ብዝኃ ተግባራትን በብቃትና በቁርጠኝነት በመፈጸም እና በማስፈጸም በሁሉም ረገድ የታለሙ ተግባራትን በሙላት በመተግበር ለማሳካት የተቀናጀ ርብርብ እንዲያደርግ ከአደራ ጭምር በማሳሰብ ስብሰባውን አጠቃለዋል፡፡
በስብሰባው የክልሉ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት አባላት፤ የፓርቲ ኃላፊዎች፤ የዞን አስተዳዳሪዎች እና የሬጂዮ ፖሊስ ከተሞች ከንቲባዎች ተሳትፈዋል፡፡




