
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት የክልሉ ገቢዎች ቢሮ 2018 በጀት አመት እቅድ አፈፃፀም እና በ2019 በጀት ዓመት እቅድ ላይ ያተኮረ የምክክር ጉባኤ በአርባምንጭ ከተማ በመካሄድ ላይ ይገኛል፡፡


ጉባኤው በክልሉ የገቢ ሴክተር የ 2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ አፈጻጸም እና በ 2019 በጀት ዓመት ዕቅድ ዙሪያ የሚወያይ ሲሆን፤ በተለይ በተጠናቀቀው የበጀት ዓመት በዘርፉ የተሰሩ ስራዎችን በመገምገም ጥንካሬዎችን ለማስቀጠል እና ለ2019 በጀት ዓመት የተሻለ አፈጻጸም ክፍተቶችን ለይቶ ለማረም የጎላ ፋይዳ ይኖረዋል፡፡


በመድረኩ የተገኙት ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በክልሉ የገቢውን ዘርፍ ያለፈ አፈጻጸም በመገምገም እና በ2019 ዕቅድ ዙሪያ ከዘርፉ አመራሮችና ባለድርሻ አካላት ጋር በመምከር፤ በዘመኑ ከታቀደው በላይ ገቢ በመሰብሰብ በራስ አቅም የልማት ጥያቄዎችን በብቃት ለመመለስ የሚያስችሉ ቀጣይ አቅጣጫዎች ያስቀምጣሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡



የክልሉ መንግስት ኢኮኖሚው ከሚያመነጨው ሀብት ፍትሀዊ ገቢን በአግባቡ በመሰብሰብ 75 በመቶ የወጪ ፍላጎትን በውስጥ አቅም ከመሸፈን ባለፈ የክልሉን ህዝብ አዳጊ የልማት ጥያቄዎች በራስ አቅም በብቃት በመመለስ ፍትሃዊ ተጠቃሚነቱን ለማረጋገጥ ለገቢ ዘርፍ ልዩ ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ላይ ይገኛል።
ለዚህም ባለፉ ጊዜያት በክልሉ የገቢ አሰባሰብ ስርዓቱ ላይ ተከታታይ የማሻሸያ የሪፎርም ስራዎችን በመስራት፤ የዘርፉን ተቋማዊ አቅም በማጎልበት እና በቴክኖሎጂ የታገዘ አሰራር በመዘርጋትና የታክስ ስርዓቱን በማዘመን በክልሉ የገቢ ዘርፍ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ ተችሏል፡፡
በዚህ ረገድ፤ በ2018 የበጀት ዓመት በአጠቃላይ ከ 32 ቢሊዮን 354 ሚሊዮን ብር በላይ ገቢ በመሰብሰብ የዘመኑን ዕቀድ ሙሉ በሙሉ ማሳካት መቻሉ፤ በክልሉ በገቢው ዘርፍ የተከናወኑ ዘርፈ ብዙ የማሻሻያ ስራዎች ውጤታማነት የሚያሳይ ከመሆኑም በላይ ለቀጣይ የዘርፉ የተሻለ አፈጸጸም አቅም የሚፈጥር ነው፡፡


ከዚህ ጋር በተያያዘ በመካሄድ ላይ ባለው ጉባኤ፤ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት የተሻለ አፈፃፀም ላስመዘገቡ መዋቅሮች እውቅና ይሰጣል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
በጉባኤዉ ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩን ጨምሮ የክልሉ መንግስት ከፍተኛ አመራሮች፣ የዘርፉ የስራ ኃላፊዎች፣ ባለድርሻ አካላት እና ጥሪ የተደረገላቸው እንግዶች በመካፈል ላይ ይገኛሉ።




