የክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት የክልሉን መንግስት የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ በሙሉ ድምፅ አፀደቀ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በምክር ቤቱ 2ኛ ቀን ውሎ፤ የክልሉን መንግስት የ2019 በጀት ዓመት ጠቋሚ ዕቅድ ያቀረቡ ሲሆን፤ ምክር ቤቱ ዕቅዱን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

ባቀረቡት ጠቋሚ ዕቅድ በበጀት ዓመቱ የተቋማት የማስፈፀም አቅም ግንባታ፣ ግብርናን በማዘመን ምርታማነትን ማላቅ፤ ሰላምና ፀጥታ፤ የቱሪዝም መዳረሻዎች ልማት፣ የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ልማት እንዲሁም ቅድሚያ የሚሰጣቸው ክልላዊና ዞናዊ ፕሮጀክቶችን ከዳር ማድረስ የትኩረት የሚሰጣቸው መሆኑን ገልፀዋል፡፡

በተጨማሪም ሀገራዊ ኢንሼቲቮች ትግበራ፣ የከተሞች እና የገጠር የኮሪደር ልማት፣ የዲጂታል ኢትዮጵያ 2030 ዕቅድ ስኬት ወሳኝ የሆኑ የፋይዳና ሌሎች ዲጂታል ተግባራት፣ ሰው ተኮር ተግባራት እንዲሁም የገቢ ስራን ማጠናከር የዕቅዱ የትኩረት አቅጣጫዎች አካል መሆናቸውን አስታውቀዋል።

በበጀት ዓመቱ ፕሮጀክቶች በተቀመጠላቸው ጊዜ በጥራት እንዲጠናቀቁ ትኩረት የሚሰጥ መሆኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከምርጫ ማግስት ጠንካራ መንግስት በሚል የተጀመረው ጎዞ ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከዚህ ባለፈ በበጀት ዓመቱ የበጎ ፈቃድ ተግባራት የሁልጊዜ ባህል ሆኖ እንዲቀጥል በማድረግ፤ በተለይ በክረምቱ  ወራት ወጣቶችን በማሳተፍ እገዛ ለሚያስፈልጋቸው ወገኖቻችን መድረስ ትኩረት ሊሰጠዋል ይገባል ብለዋል።

ዕቅዱን በመደመር መንግስት የመፍጠር፤ የመፍጠንና የመዝለል እሳቤና መርህ ለመፈጸም ዝግጅት መደረጉን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ አመራሩ በመተጋገዝ፣ በቅንነት፣ የውስጥ አንድነትን በማጠናከር እና በመደጋገፍ  ለዕቅዱ ስኬት መረባረብ እንደሚገባው አሳስበዋል።  

ርዕሰ መስተዳድሩ ያቀረቡት የክልሉ መንግስት የ2019 በጀት አመት ጠቋሚ ዕቅድ ተከትሎ፤ የምክር ቤት አባላት ጠቋሚ ዕቅዱን በተመለከተ አስተያየትና ጥያቄዎችን አቅርበው በርዕሰ መስተዳድሩ ማብራሪያ የተሰጠባቸው ሲሆን፤ ምክር ቤቱ ዕቅዱን በሙሉ ድምፅ አፅድቋል፡፡

Leave a Reply