
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በወላይታ ሶዶ ከተማ ባካሄደው 17ኛ መደበኛ ስብሰባው በልዩ ልዩ አጀንዳዎቸ ላይ ተወያይቶ የተለያዩ ውሳኔዎችን አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በ17ኛ መደበኛ ስብሰባው የክልሉን የ2017 የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀምና ቀጣይ አቅጣጫዎች በተመለከተ፤ የተለያዩ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶችን እና ሌሎች ተያያዥ የካቢኔ ውሳኔ የሚሹ አጀንዳዎች ላይ በመመከር ውሳኔ አሳልፏል፡፡



ምክር ቤቱ በቅድሚያ የክልሉን መንግስት የሩብ ዓመት ዕቅድ አፈፃፀም የገመገመ ሲሆን፣ ከተያዘው ግብ አንፃር ጥንካሬዎችን ማስቀጠል እና ክፍተቶችን ለይቶ ለቀጣይ ሩብ ዓመት አቅጣጫ ለማስቀመጥ የሚያስችል ሰፊ ውይይት አድርጓል።
በሩብ ዓመቱ በክልሉ የማስፈፀም አቅምን ከፍ የሚያደርጉ ቁልፍ ግቦችን በማስቀመጥ፣ አቅምን ያገናዘበ ዕቅድ እና የፈፃሚ ዝግጅቶችን አድርጎ ወደ ተልዕኮ በመግባት አመርቂ ስራዎች መሰራታቸው ተገምግሟል።



በክልሉ በጎፋ ዞን የጋጠመው የተፈጥሮ አደጋ በሩብ ዓመቱ ያገጠመ ተግዳሮት መሆኑ የተመለከተ ሲሆን፣ የአደጋው ተጎጂዎችን ከሁለት ወር ባነሰ ጊዜ ወደ ቋሚ መጠለያ ማሻገር መቻሉ በስኬት የሚወሰድ መሆኑ ተገልጿል።
በክልሉ በወርሃ መስከረም የተከበሩ የብሄረሰብ የዘመን መለወጫ በዓላት፣ ወንድማማችነትንና ሕብረ-ብሔራዊነትን ባጎለበተ መልኩ፣ ባህላዊ እሴታቸውን ጠብቀው በሰላም መከበራቸው፣ ክልሉ እያከናወነ የሚገኘውን የህዝብ ለህዝብ ትስስር ስራዎች ውጤታማነት የሚያሳይና የሚያጠናክር መሆኑም ተመላክቷል።



ክልሉ በሩብ ዓመቱ ምርታማነትን በማሳደግ ከተረጂነት ለመላቀቅ በሚደረገው ጥረት፣ በመኽር እርሻ የሰብል ምርታማነት ወደ ላቀ ደረጃ ለማሸጋገር ልዩ ትኩረት በመስጠት በተሰሩ ስራዎች፣ አመርቂ ውጤት ከወዲሁ በመታየት ላይ መሆኑም ተመልክቷል።
በቀጣይ፣ ከወቅቱ የዝናብ ሁኔታ አንጻር፣ የደረሰ የሰብል ምርት ለጉዳት እንዳይዳረግ ያለብክነት በዘመቻ የመሰብስ ስራን ጨምሮ ለቀሪ የመኽር እርሻ ስራዎች ተገቢው ትኩረት በመስጠት ለተያዘው ግብ ስኬት ርብርብ እንዲደረግ ምክር ቤቱ አቅጣጫ አስቀምጧል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በቀጣይም:- ለግብርና ልማት ስራዎች፣ በንቅናቄ የሚከናወኑ ተግባራት፣ የዋጋ ንረት ቁጥጥርና ክትትል፣ የስራ ዕድል ፈጠራ ተግባራት፣ የኮዲንግ ስልጠና፣ የኮሪደር ልማት፣ የትምህርት ስራዎች፣ በጤናው ዘርፍ የበሽታ መከላከል ስራዎች፣ የገቢ አሰባሰብ ስራን የማጠናከር በቀጣይ ልዩ ትከረት ሊሰጣቸው እንደሚገባ አቅጣጫ አስቀምጧል።



መስተዳድር ምክር ቤቱ ኢንቨስትመንትን በተመለከተ አጀንዳው የክልሉን ፀጋዎች ተጠቅሞ በክልሉ ፈጣን ዕድገት በማስመዝገብ የህዝቡን ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ የግል ባለሀብቱን በተለያዩ የኢንቨስትመንት ዘርፎች በማሰማራት ውጤታማ ስራ በመስራት ላይ መሆኑም ተገልጿል።
በክልሉ በኢንዱስትሪ፣ በማንፋክቸሪንግ፣ በግብርና እና በአገልግሎት ዘርፍ ለማልማት ጥያቄ ባቀረቡ አልሚ ባለሀብቶች ዙሪያ በመወያየት መስፈርቱን አሟልተው ለተገኙ አልሚዎች መስተዳድር ምክር ቤቱ ፈቃድ እንዲሰጥ ውሳኔ አስተላልፏል።
በተጨማሪም መስተዳድር ምክር ቤቱ ሌሎች የካቢኒ ውሳኔ የሚሹ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ በመወሰን ስብሰባውን አጠናቋል።