
ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ ክልላዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን በማረጋገጥ ለማብሰር በየደረጃው ባሉ መዋቅሮች በመከናወን ላይ የሚገኙ ተግባራት ያሉበት ደረጃን በበይነ መረብ በመገምገም ለታለመው ግብ ስኬት ቀጣይ አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡፡
በስብሰባው የክልሉ የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ኮሚሽነር ወገኔ ቡዙነህ፤ በክልሉ የሰብዓዊ ድጋፍ ሉዓላዊነትን ለማብሰር የተከናወኑ ተግባራትን የተመለከተ ዝርዝር ሪፖርት አቅርበው ሰፊ ውይይት ተደርጎበታል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በዚሁ ወቅት፤ እንደ ሀገር ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት ለመሸጋገር የተጀመረውን ጉዞ እስከ ታህሳስ 2019 ዓ/ም በውጤታማነት በመፈፀም ከግብ ለማድረስ አቅጣጫ መቀመጡን አስታውሰዋል።
አክለው በክልሉም በተመሳሳይ እንደ ሀገር በወጥነት ለማሳካት ለታለመው ግብ ስኬት፤ የኢኮኖሚ ሉዓላዊነትን በማስጠበቅ ከተረጂነት ለመላቀቅ እና በተያዘው ጊዜ ውስጥ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን የሚያስችል አቅም በመገንባት ለማብሰር በተደራጀና በተቀናጀ አግባብ ወደ ስራ መገባቱን ገልፀዋል፡፡
በዚህ ረገድ ባለፉ ጊዜያት በየዞኑ የተከናወኑ ተግባራት አበረታች መሆናቸውን የገመገሙት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ከተረጂነት ወደ ምርታማነት ለተሟላ ሀገራዊ ክብርና ሉዓላዊነት የሚደረገውን ጉዞ ከግብ በማድረስ ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን ቀዳሚ አጀንዳ መሆኑን በመገንዘብ በትኩረት መስራት እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለስራው ስኬታማነት ተግባራትን በተቋማዊ ማዕቀፍና አሰራር በመምራት ውጤታማነታቸውን መከታተል ወሳኝ መሆኑንም ጠቅሰው፤ ለዚህ ከክልላዊው ምክር ቤት እና ዐቢይ ኮሚቴ በተጨማሪ የዞን አስተዳዳሪዎችና የከተማ አስተዳደር ከንቲቦች ተግባራትን በቅርበት በመከታተል በትኩረት መምራት እንደሚገባቸው አሳስበዋል፡፡
በተለይ በተያዘው ክረምት በንቅናቄ ከሚመሩ ተግባራት ከተረጂነት ወደ ምርታማነት የሚደረገውን ሽግግር በማጠናከር ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም መሸፈን ቀዳሚ ሊሆን ይገባል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ለውጤታማነቱ የተቀመጡ ስትራቴጂዎችን እና የማስፈጸሚያ ስልቶች በሙሉ አቅም ገቢራዊ ማድረግ እንደሚገባ ተናግረዋል፡፡
ለዚህ የሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የማረጋገጥ ተግባራትን ለመምራት የተቀመጡ መርሆችን – አካታችነት፤ አሳታፊነት፤ ቅንጅት፤ ጥራት፤ ዘላቂነትና እውነተኛነትን ከማስፈፀሚያ ስትራቴጂዎች ጋር አቀናጅቶ በመተግበር እንደ ክልል ለሚታወጀው ሰብዓዊ ድጋፍን በራስ አቅም የመሸፈን ስኬት በቁርጠኝነት መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል።


ርዕሰ መስተዳድሩ በስትራቴጂው መሰረት በራስ አቅም የሰብዓዊ ድጋፍ ማድረግ የሚያስችል ተቋማዊ አቅም ለመገንባት በተለየ ትኩረት ለሰራባቸው የሚገቡ የሚከተሉት የትኩረት አቅጣጫዎችን አስቀምጠዋል፡-
*መረጃ መለየትና ማጥራት፡- ከተረጂዎች ልየታ አንጻር ድጋፍ የሚሹ ዜጎችን እሰከ ታችኛው መዋቅር በአግባቡ በመለየት መረጃን ማጥራትና ማደረጃት ይገባል፤
*የመጠባበቂያ እህል ክምችት፡-በዞን፤ በወረዳ እና በከተማ አስተዳደር ደረጃ ደረጃቸውን የጠበቁ መጋዝኖችን በማዘጋጀት፤ ሳይበላሹ መቆየት የሚችሉ ሰብሎችን በመሰብሰብ ምላሽ መስጠት የሚያስችል የመጠባበቂ እህል ክምችት ማዘጋጀት፤
*የስትራቴጂክ እህል ክምችት፡- በተፈጥሮና ሰው ሰራሽ አደጋዎች ተጋላጭ ለሚሆኑ ዜጎች በራስ አቅም ምላሽ መስጠት የሚያስችል ምግብ ነክና ምግብ ነክ ያልሆኑ ክልላዊ የሰብዓዊ ድጋፍ ክምችት ማዘጋጀት፤
*የአደጋ ጊዜ መጠባበቂያ ፌንድ፡- በተዘረጋው የህግና የአሰራር ማዕቀፍ መሰረት ሁሉንም የህብረተሰብ ክፍሎች ባሳተፈ መልኩ የመጠባበቂያ ፌንድ መሰብሰብና ማስተዳደር ይገባል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ በተጨማሪም በተለይ በበልግ ወቅት በተወሰኑ የክልሉ አካባቢዎች ያጋጠመ የዝናብ ዕጥረትን ከግምት በማስገባት በመኽር አዝመራ በአጭር ጊዜ ሊደርሱ ለሚችሉ ሰብሎች ትኩረት ሰጥቶ መስራትን ጨምሮ ተያያዥ አፋጣኝ የመፍትሄ አቅጣጫዎችን በማስቀመጥ መድረኩን አጠቃለዋል።


በውይይቱ የክልሉ የአደጋ ስጋት ምክር ቤት አባላት፤ የፓርቲ ኃላፊዎች፤ የዞን አስተዳዳሪዎች እና የሬጂዮ ፖሊስ ከተሞች ከንቲባዎች ተሳትፈዋል፡፡




