በክልሉ የገጠር ኮሪደር ልማት የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ በማዘመን ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ በመተግበር ላይ ይገኛል- ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በክልሉ ሀገራዊው የገጠር ኮሪደር ልማት ኢኒሼቲቭ፤ የአርሶና አርብቶ አደሩን የኑሮ ዘይቤ ለማዘመን እና በተቀናጀ የገጠር ልማት የታለመውን የገጠር ሽግግር ዕውን በማድረግ ሁለንተናዊ ብልጽግናን ለማረጋገጥ በሚያስችል አግባብ ወደ ትግበራ መግባቱን ገልፀዋል፡፡

እንደ ሀገር በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ አስጀማሪነት የተጀመረው ኢኒሼቲቩ፤ በዋናነት የገጠሩን ማኅበረሰብ የኑሮ ዘይቤ የማሻሻል፣ ምርታማነትን የማሳደግ እንዲሁም አርሶና አርብቶ አደሩ የተሻለ ሕይወት እንዲመራ በማስቻል መሠረታዊ ለውጥ ለማምጣት ያለመ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

ከሀገራዊ ለውጡ በፊት የገጠሩ አካባቢ በልማቱ ረገድ ተገቢው ትኩረት ተነፍጎት መቆየቱን የጠቀሱት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ የለውጡ መንግስት ከፍተኛ ቁጥር ያለው ሕዝብ ለሚኖርበት የገጠሩ ክፍል ተገቢውን ትኩረት ሰጥቶ በመስራት ተጨባጭ ለውጥ በማስመዝገብ ላይ ይገኛል ብለዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ የገጠር አካባቢዎችን በዘመናዊ መሠረተ ልማት በማስተሳሰር የገጠሩን ማኅበረሰብ ፍትሃዊ የልማት ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ገጠሩን ወደ ልማት ማዕከልነት በማሸጋገር ወደ ዘመናዊ የብልጽግና መሠረትነት የመቀየር ትልምን ያነገበ መሆኑንም አስገንዝበዋል፡፡  

ርዕሰ መስተዳድሩ በክልሉ ለኢኒሼቲቩ ውጤታማ አተገባበር በክልላዊ የዘጠና ቀን ዕቅድ በማካተት እንዲሁም በተደራጀ ተቋማዊ ማዕቀፍ መምራት የሚያስችል አደረጃጀትና አሰራር በመዘርጋት እና አካባቢያዊ ነባራዊ ሁኔታን ከግምት ያስገባ ማስተር ፕላን በማዘጋጀት አስፈላጊው ዝግጅት ተደርጎ ወደ ትግበራ መገባቱንም ገልፀዋል፡፡

በሞዴል ደረጃ ተጀምሮ በተለያዩ ምዕራፎች ለማስፋት የታቀደው ኢኒሼቲቩ፤ በመጀመሪያው ምዕራፍ- በወላይታ ዞን፤ በጋሞ ዞን እና በጌዴኦ ዞን የኮሪደር ልማቱ አካል ለሆነው ሞዴል የገጠር መንደር ግንባታ ትኩረት በመስጠት፤ በእያንዳንዱ ዞን ለመነሻ አምስት አምስት ቤቶችን ለመገንባት ታልሞ ወደ ተግባራዊ ስራ መገባቱንም አስረድተዋል፡፡    

በትግበራው ሂደት በተለይ በቤቶች ግንባታ ከዚህ ቀደም በሌሎች አካባቢዎች ከነበረው ሀገራዊ ተሞክሮ በተለየ በሞዴል አርሶ አደሮች ቀጥተኛ ተሳትፎ እና ባለቤትነት መከናወኑን የገለፁት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ይህም በክልሉ የገጠር ኮሪደር ልማቱን በፍጥነት ለማስፋፋት አስትዋጽኦው የጎላ መሆኑን ተናግረዋል፡፡

በዚህ ረገድ የጋሞ ዞን አስተዳደር፤ በዞኑ በምዕራብ አባያ ወረዳ በራስ ተነሳሽነት ሞደል አርሶ አደሮችን በማስተባበር ተጨማሪ 12 ቤቶችን ሙሉ የገጠር ፓኬጆችን ባሟላ መልኩ ገንብቶ በማጠናቀቅ ምሳሌ መሆን የሚችል ሥራ መስራቱንም ጠቅሰው፤ ሌሎች ዞኖች ይህን ተሞክሮ ማስፋት ይገባቸዋል ሲሉ አሳስበዋል፡፡ 

ርዕሰ መስተዳድሩ በቅርቡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ/ር)፤ በክልሉ ባደረጉት የስራ ቆይታ፤ በምዕራብ አባያ ወረዳ በይፋ የመረቁት “የሀማሳ ኢልሎ ሞዴል የገጠር መንደር” የዚሁ ስራ ውጤት መሆኑንም ገልፀዋል፡፡    

በክልሉ የመጀመሪያ የሆነው ይሄው ሞዴል መንደር፤ ቀላል ወጪ በሚጠይቁና በአካባቢው የሚገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም፤ በመደመር መንግስት የመፍጠንና የመፍጠር መርህ፤ በጠንካራ ድጋፍና ክትትል በልዩ ትኩረት በመምራት ከተያዘው ጊዜ ቀድሞ በሁለት ወር ጊዜ ውስጥ ማጠናቀቅ መቻሉንም ተናግረዋል፡፡ 

በ79.4 ሄ/ር መሬት ላይ ያረፈው ይህ ዘመናዊ መንደር፤ የአርሶ አደሩን ኑሮ ለማዘመን የሚያግዙ ዘመናዊ መኖሪያ ቤቶች፤ የእንስሳት ማደሪያ፣ የአትክልት ስፍራ፣ ከታዳሽ የሶላር ኢነርጂና ባዮ ጋዝ አስተማማኝ የሃይል አቅርቦት፤ የንፁህ ውኃ፣ የጤና እና የትምህርት መሠረተ ልማቶችንና ሌሎች አገልግሎቶች ያካተተ መሆኑንም ገልፀዋል፡፡

ከዚህም ባለፈ መንደሩ አርሶ አደሩ የጓሮ አትክልትና ፍራፍሬ ልማትን ከሌማት ትሩፋት የዶሮ፤ የወተት ላምና የፍየል እርባታ የእንስሳት ሀብት ልማት እንዲሁም የንብ ማነብ የማር ምርት ልማት ጋር አቀናጅቶ በመተግበር በተቀናጀ የግብርና ልማት ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነቱን ወደ ላቀ ደረጃ የሚያሸጋግር መሆኑንም አስረድተዋል፡፡

ርዕሰ መስተዳድሩ በአስፈላጊው መሠረተ ልማትና የማህበራዊ አገልግሎት መስጫ ተቋማት ተሳስረው የሚገነቡ ሞዴል መንደሮች፤ የገጠሩ ማኅበረሰብ ባህልና ወጉን ጠብቆ ክብር ያለው ኑሮ እንዲኖር የሚያስችሉ ከመሆኑም በላይ የገጠር ሽግግር ማዕከላት በመሆን ወደ ሁለንተናዊ ብልጽግና የሚደረግ ጉዞን የሚያሳልጡ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡

የኮሪደር ልማቱ ከስራ ዕድል ፈጠራ እና ከቴክኖሎጂ ሽግግር አኳያም አመርቂ ውጤት የተመዘገበበት መሆኑን ጠቅሰው፤ በተለይ ከዚህ ቀደም ባልተለመደ መልኩ ለቤት ግንባታ የአፈር ጡብ በማምረት መጠቀም መቻሉና ለወጣቶች በጡብ ማምረት፤ በግብዓት አቅርቦትና በቤት ግንባታ ሰፊ የስራ ዕድል መፍጠር መቻሉን ገልፀዋል፡፡ 

በክልሉ የመጀመሪያ ምዕራፍ የገጠር ኮሪደር ልማት የተገኘው አመርቂ ስኬት፤ የገጠሩን ማኅብረሰብ ኑሮ ለማዘመን በቁርጠኝነት ከተሰራ ባጠረ ጊዜ፣ በውስን ቦታና ሀብት የገጠሩን አካባቢ ማዘመንና መለወጥ እንደሚቻል ማሳያ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም በተለያዩ ምዕራፎች ይሄው ተጠናክሮ የሚቀጥል መሆኑን አረጋግጠዋል፡፡

Leave a Reply