
የደቡብ ኢትዮጵያ ክልል መንግስት መስተዳድር ምክር ቤት በ31ኛ መደበኛ ስብሰባው፡- በክልሉ መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈፃፀምና በቀጣይ የ2019 በጀት ቀመር የዝግጅት ሂደት ላይ፣ አዋጆችን መርምሮ ማፅደቅ እንዲሁም ሌሎች የካቢኔ ውሳኔ በሚሹ ጉዳዮች ላይ በመወያየት ወሳኔ አሳልፏል።


ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው በክልሉ መንግስት የ2018 በጀት ዓመት አጠቃላይ የስራ አፈፃፀም ዙሪያ ሲሆን፡- የክልሉን አስፈጻሚ ተቋማት የበጀት አመቱን የስራ አፈፃፀም የዳሰሰ ዝርዝር ሪፖርት ቀርቦ ከተያዘው ግብ አንፃር በመገምገም የነበሩ ጥንካሬዎች፤ የተገኙ ስኬቶችንና ያጋጠሙ ተግዳሮቶችን በመለየት በጥልቀት ተወያይቷል፡፡
በውይይቱ በበጀት ዓመቱ የክልሉን ህዝብ ፍትሃዊ ተጠቃሚነት ከማረጋገጥ ባለፈ ክልላዊና ሀገራዊ የሰላም፤ የልማትና የብልጽግና ትልሞችን ዕውን ለማድረግ አቅም የፈጠሩ ዘርፈ ብዙ የሰላምና ፀጥታ፤ የመልካም አስተዳደር እንዲሁም የማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ የዕድገትና የልማት ስራዎችና ፖለቲካዊ ተግባራት መከናወናቸው ተገምግሟል፡፡



በተለይ በዋና ዋና የማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ የትኩረት ዘርፎች፤ በሰው ተኮር ተግባራት እንዲሁም በመደበኛና በንቅናቄ በሚመሩ ሀገራዊና ክልላዊ የልማት ኢኒሼቲቮች ትግበራ አመርቂ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተመልክቷል፡፡
በተለይ ከሰላምና ፀጥታ አኳያ 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫው ያለምንም የፀጥታ ችግር በስኬት መጠናቀቅ መቻሉ እንዲሁም በራስ አቅም የተለያዩ የሰላም ግንባታ እና የቅደመ ግጭት መከላከል ስራዎች ላይ ትኩረት ተደርጎ ስኬታማ ስራዎች መሰራታቸውን በመግለፅ ምክር ቤቱ ለፀጥታ መዋቅር አመራሮችና ባለሙያዎች ዕውቅና ሰጥቷል፡፡
በተጨማሪም በበጀት ዓመቱ ወጪን በመቀነስ ገቢን የማሳደግ ስራ እንዲሁም የሀብት ውስንነቶችን በመቋቋም እና ጊዜና ወጪ ቆጣቢ አሰራሮችን በመዘርጋት በተሰሩ ስራዎች ውጤታማ መሆን መቻሉም በውይይቱ ተነስቷል፡፡
ምክር ቤቱ በበጀት ዓመቱ በክልሉ በግብርና ልማት፤ በኢንዱስትሪና በማዕድን ልማት፤ በከተሞች ልማትና የመሠረተ ልማት ስራዎች፤ በንጽሁ የመጠጥ ውሃ ሽፋንና መንገድ ግንባታ፤ በትምህርትና ጤና የማህበራዊ ልማት መስኮች፤ በስራ ዕድል ፈጠራና በሌሎችም ዘርፎች አመርቂ ውጤት መመዝገቡን ገምግሟል፡፡

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በዚሁ ወቅት፤ 2018 የበጀት ዓመት፤ በክልሉ ህዝብ ግንባር ቀደም ተሳትፎና በአመራሩ የተቀናጀ ርብርብ በየአካባቢው ያሉ ፀጋዎችን ገልጦ ለመጠቀም በተደረጉ ጥረቶች በሁሉም መስክ ለሀገራዊና ክልላዊ የዘላቂ ሰላምና የብልጽግና ግብ ስኬት መሠረት የጣሉ ውጤቶች የተገኙበት መሆኑን ገልፀዋል፡፡
በፖለቲካው ረገድ፤ በ7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊና ክልላዊ ምርጫ በቅድመ ምርጫ፤ በምርጫና በድህረ ምርጫ በተከናወኑ ውጤታማ ተግባራት፤ በዴሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ጉዟችን አዲስ ምዕራፍ የከፈተ፤ ኢትዮጵያና መላው ህዝቦቿን አሸናፊ ያደረግ ታሪካዊ ውጤት ማስመዝገብ መቻሉ ተጠቃሽ መሆኑንም ተናግረዋል፡፡
በክልሉ ያሉ ፀጋዎችን በመጠቀም በሁሉም መስክ ምርታማነትን ማሳደግና ተረጂነትን ታሪክ ማድረግ እንዲሁም የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ማረጋገጥ የህልውና ጉዳይ ነው ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በቀጣይም እንደ ሀገር በወጥነት ሊሳኩ በሚገቡ የልማት ኢኒሼቲቮችና በዋና ዋና የትኩረት ዘርፎች የላቀ ውጤት ለማስመዝገብ መስራት እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡
ርዕሰ መስተዳድሩ አክለው በመጀመሪያ ምዕራፍ በተከናወኑ የገጠር ኮሪደር ልማት ስራዎች በተለይ በጋሞ ዞን በሞዴል አርሶ አደሮች በተሰራው ሞዴል የገጠር መንደር እንደ ሀገር ክልሉ እውቅና ያገኘበት ታላቅ ተግባር መሆኑን ጠቅሰው፤ ቀሪ ዞኖች ላይ ተጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባ በአጽንኦት ገልፀዋል።



በመጨረሻም መስተዳድር ምክር ቤቱ የክልሉን መንግስት የ2018 በጀት ዓመት ዕቅድ አፈጻጸም ሪፖርት ከነማሻሻያው በማፅደቅ፤ ለክልሉ ሕዝብ ምክር ቤት እንዲመራ በሙሉ ድምፅ ውሳኔ አሳልፏል።
መስተዳድር ምክር ቤቱ በመቀጠል የተወያየው በክልሉ መንግስት የ2019 በጀት ዓመት የበጀት ቀመር ድልድል መነሻ ሃሳብ ላይ ሲሆን፤ የቀረበውን ረቂቅ የበጀት ቀመር ድልድል ታዓማኒነትና አሳታፊነትን ባማከለ መልኩ የሀብት ክፍፍል ከማድረግ፤ በክልሉ መሪ የልማት ዕቅድ ላይ የተቀመጡ ግቦችን ከማስፈፀም፤ ሀገራዊና ክልላዊ የዘላቂ ሰላምና የሁለንተናዊ ብልፅግና ራዕይን ዕውን ለማድረግ የተጀመሩ ጥረቶች ከማጠናከር እንዲሁም ከኢፌዲሪ ፌዴሬሽን ም/ቤት የበጀት ድልድል ቀመር አኳያ በመገምገም በዝርዝር ተወያይቷል፡፡
ምክር ቤቱ በመጨረሻም የህዝብ የልማት ጥያቄዎችን በቅርበት ተደራሽ ከማድረግ አኳያ ከጠቅላላው የክልሉ መንግስት የ2019 በጀት ውስጥ:- 20 በመቶውን ለክልል ማዕከላት እንዲሁም 80 በመቶውን ለዞን ዕርከኖች እንዲውል በሙሉ ድምፅ በመወሰን የውሳኔ ሃሳቡን ለክልሉ ብሔረሰቦች ምክር ቤት መርቷል።
ምክር ቤቱ በተጨማሪም ወቅታዊ የግብርና ልማት ስራዎች በተለይም የኤሊኖን ክስተት ከግምት ያስገባ የመኽር እርሻ ዝግጅት፤ በክረምት በንቅናቄ የሚከናወኑ የአረንጓዴ አሻራና የበጎ ፈቃድ አገልግሎት ሰው ተኮር ተግባራት፤ የከተሞች ፅዳትና የአረንጓዴ ልማት፤ የልማት ኢኒሼቲቮች ውጤታማ ትግበራ እንዲሁም የአደጋ ስጋት ስራ አመራር ተግባራት የሚያጠናከሩ ቀጣይ አቅጣጫዎች በማስቀመጥ ስብሰባውን አጠናቋል፡፡




