“አይቀሬ የሆነው የኢትዮጵያን ብልፅግና በማረጋገጥ የተሻለች ተምሳሌታዊ ሀገር እናሻግራለን” ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ

ርዕሰ መስተዳድር ጥላሁን ከበደ በተገኙበት 7ኛውን ሀገራዊ ምርጫ አስመልክቶ የብልፅግና ፓርቲ የምርጫ ቅስቀሳና የድጋፍ ሰልፍ በጎፋ ዞን፤ በሳውላ ከተማ በከፍተኛ ህዝባዊ ተሳትፎ በድምቀት ተካሂዷል፡፡  

በመርሃ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት ክቡር ርዕሰ መስተዳድሩ፡-ብልፅግና ባለፉት የለውጥ ዓመታት አይቀረ የሆነው የኢትዮጵያን ብልፅግና በማይቀለበስ መሠረት ላይ ማስቀመጥ የቻሉ፤ በርካታ ማህበራዊ፤ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ስኬቶች ማስመዝገብ መቻሉን ተናግረዋል፡፡

ፓርቲው በጠራ ራዕይ እየተመራ ሁለንተናዊ ብልፅግናዋ የተረጋገጠ፤ለትውልድ ለማሻገር በመትጋት ላይ ይገኛል ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዚህም በሁሉም የልማት አውታሮች የኢትዮጵያን የንጋት ዘመን ጅማሮ ያበሰሩ፤ ቃልን በተግባር ያረጋገጡ አመርቂ ስኬቶች ማስመዝገቡን ገልፀዋል፡፡

ክልሉን የሰላም፤ የመቻቻልና የብልጽግና ተምሳሌት የማድረግ ራዕይ የሰነቀው የክልሉ መንግስት፤ ባለፉት ዓመታት የህዝቡን ሁለንተናዊ ተጠቃሚነት ያረጋገጡና ለሀገራዊና ክልላዊ የብልፅግና ግብ ስኬት መሠረት የጣሉ ዘርፈ ብዙ ስኬቶችን ማስመዝገብ መቻሉንም አያይዘው ተናግረዋል፡፡

ሰላማችንን ጠብቀን በሁሉም የልማት መስኮች እጅ ለእጅ ተያይዘን በኅብረትና በአንድነት ተባብረን ከሰራን የምንሻውን ዕድገትና ልማት በአጭር ጊዜ ዕውን ማድረግ እንችላለን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ ህብረተሰቡ ሰላሙን ጠብቆ በማቆት በሙሉ አቅሙ የልማት ትብብሮችን ሊያጠናክር እንደሚገባ አሳስበዋል፡፡  

ግንቦት 24 የሀገራችንን የዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ የሚናፀናበት ታሪካቂ ቀን ያሉት ርዕሰ መስተዳድሩ፤ በዕለቱ ሁሉም የመራጭነት ካርድ የወሰደ ዜጋ በነቂስ ወጥቶ የስንዴ ነዶን በመምረጥ የተጀመረውን ልማት በማስቀጠል ኢትዮጵያን ወደ ብልፅግና የማሻገር ራዕይ እውን እንዲያደርጉ ጥሪ አቅርበዋል።

በሕ/ተ/ም/ቤት የመንግስት ተጠሪ ሚኒስትር ተስፋዬ በልጅጌ (ዶ/ር) በበኩላቸው፤ በብልፅግና መራሹ መንግስት ባለፉት ስምንት ዓመታት ደቡብ ኢትዮጵያ ክልል እንዲሁም ጎፋ ዞን እንደ አዲስ የተወለዱበት መሆኑን ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ በተስፋ የተሞላች ሀገር መሆኗን የገለፁት ሚኒስትሩ፤ ብልፅግና ፓርቲ ሀገራችንን የአፍሪካ የብልፅግና ተምሳሌት ለማድረግ ይዞት የተነሳውን ራዕይ ዕውን በማድረግ ኢትዮጵያን ወደ ከፍታ ማድረስ እንዲቻል የተጀመሩ ስራዎችን ለማስቀጠል ብልፅግናን ይምረጡ ሲሉ ጥሪ አቅርበዋል።    

የክልሉ ብልፅግና ፓርቲ ቅ/ጽ/ቤት ኃላፊ አቶ ገብረ መስቀል ጫላ በበኩላቸው፤ ብልፅግና ለዜጎች ሰብዓአዊ መብቶችና መሰረታዊ ፍላጎቶች እንዲሟሉ የሚተጋ፤ የሚናገረውን በተግባር የምፈፅም፤ የእንዲሁም ትውልድ ፅናትና የሀገሬ ክብር የሚገለፅበት ፓርቲ መሆኑን ተናግረዋል።

ፓርቲው ባለፉት ስምነት ዓመታት ለዜጎች መበልፀግ ተግቶ በመስራት የሚታይ የሚጨበጥ ለውጥ ማምጣት መቻሉንም ገልፀው፤ ይሄን መልካም ስራ ለማስፋት እና የተጀመረውን ልማት አጠናክሮ ለማስቀጠል ብልፅግናን መምረጥ እንደሚገባ አስገንዝበዋል።       

ምርጫ ዜጎች የዜግነት መብታቸውን ተጠቅመው በሀገራቸው ጉዳይ ላይ ያላቸውን የመወሰን መብት በተግባር በመተርጎም የስልጣን ምንጭ ህዝብ መሆኑን ከማረጋገጥ ባለፈ በፀና መሠረት ላይ የተገነባች ሀገር ለትውልድ በማሻገሩ ረገድ ደማቅ አሻራቸውን በድምፃቸው የሚያኖሩበት ሂደት ጭምር ነው፡፡  

በዚህ ረገድ ግንቦት 24 በሚካሄደው 7ኛው ጠቅላላ ሀገራዊ ምርጫ፤ የመራጪነት ካርድ የወሰዱ 50 ሚሊዮን ዜጎች በምርጫው በመሳተፍ፤ በድምፃቸው መፃይ የሀገራቸውን ማህበረ-ኢኮኖሚያዊ እና ፖለቲካዊ የፖሊሲ አቅጣጫ ከመወሰን ባሻገር በኢትዮጵያ የዲሞክራሲ ጉዞ አዲስ የታሪክ ምዕራፍ ይከፍታሉ ተብሎ ይጠበቃል፡፡ 

መንግስት ባለፉት የለውጥ አመታት ለዲሞክራሲ ስርዓት ግንባታ በቁርጠኝነት በመስራት በሀሳብ ልዕልና ላይ የተመሰረተ አካታችና አሳታፊ የፖለቲካ ባህል የሚያጎለብቱ እና የመድብለ ፓርቲ ስርዓት ግንባታን የሚያጠናክሩ ተቋማዊ ሪፎርሞችን በማድረግ ጭምር ተጨባጭ ለውጥ ማስመዝገብ መቻሉ ይታወቃል፡፡

7ኛው ሀገራዊ ምርጫም የተጀመሩ ጥረቶችን በማጎልበት እንደ ሀገር ለሰነቅነው ለዲሞክራሲያዊ ስርዓት ግንባታ ማበብ አንድምታው ከፍተኛ ነው፡፡

ለዚህም መንግስት ምርጫው ፍጹም ሰላማዊ፤ ፍትሃዊ፤ ነፃና ሁለንተናዊ ሆኖ በስኬት እንዲጠናቀቅ በቁርጠኝነት ሲሰራ የቆየ ሲሆን፤ በሁሉም ረገድ በቂ ዝግጅት ማድረግ መቻሉም ታወቋል፡፡  

Leave a Reply